የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቦችን ለማጋጨት በሽብርና በጥላቻ ዘመቻ ለተሰማሩት ግለሰቦች አስጠነቀቀ

የኢትዮጵያ መንግስት የአንዱ ወይም የሌላኛው ሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል፣ ህዝቦችን ለማጋጨት በሽብርና በጥላቻ ዘመቻ ለተሰማሩት ግለሰቦች ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል ፡፡

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዛሬ በወጣው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫው የአንዱ ወይም የሌላኛው ሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል፣ በሶሻል ሚዲያና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች አማካኝነት ችግሩን በማራገብና በማጋነን፣ በሽብር እና የጥላቻ ቅስቀሳ እኩይ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ አካላት ሁሉ ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ መንግሥት ያስጠነቅቃል ነው ያለው ።

አንዳንድ አካላትም፣ በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር በመደናገጥ በደመ ነፍስ እየሰጡት ያለው መረጃ እና እርስ በርስ የመወነጃጀል ተግባር ችግሩን ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ከዚህ መሰሉ አድራጎት እንዲታቀቡ አሳስቧል ፡፡

በዚህ መሰሉ ተግባር ላይ መሳተፍ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ከባድ ወንጀል እንደሆነም መንግሥት አስገንዝቧል ፡፡

ለዘመናት አብረው የኖሩትን የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊ ወንድማማች ህዝቦችን ፈጽሞ ሊወክል የማይችል ግጭት ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ለወገኖቻችን ሞትና መፈናቀል ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል ፡፡

የሕዝቦች የቆየ ወንድማማችነት በጊዜያዊ ችግር ሳይገታ ተጠናክሮ ይቀጥላል! ነው ያለው መንግስት በመግለጫው ፡፡

በዚህ አጋጣሚ በዚህ ግጭት ሳቢያ ህይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይመኛል ብሏል ፡፡

ዝርዝር መግለጫው እነሆ

 

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም.

የሕዝቦች የቆየ ወንድማማችነት በጊዜያዊ ችግር ሳይገታ ተጠናክሮ ይቀጥላል!

 

አገራችን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ጨቅላ ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ባለፈባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ አንጸባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለ ነው። ከአሁኑ ለሌሎች ሃገራት ልምዶችን እያካፈለ የሚገኝም ስርዓት ሆኗል፡፡ አገራችን ሰላም በራቀው የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ እየኖረች፣ የራሷን ሰላም አስተማማኝ ከማድረግ አልፋ ለአካባቢውና ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የሰላም ዘብ ለመሆን የበቃችውም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወደውና ፈቅደው በመሰረቱት ፌዴራላዊ ስርዓት አማካኝነት ውስጣዊ ሰላሟን በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ በመቻላቸው ነው። ኢትዮጵያውያን እነዚህና ሌሎች በርካታ አንፀባራዊ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉት ግን መንገዳቸው ሁሉ አልጋ በአልጋ ስለሆነላቸው አልነበረም። በየወቅቱ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ሁሉ በፌዴራል ሥርዓታቸው ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በፅናት እየፈቱ በማለፋቸው እንጅ!  

በቅርቡ ካጋጠሙን ፈተናዎች መካከል አንዱ በአንዳንድ አካባቢዎች ከወሰን ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ችግሮች ይጠቀሳሉ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የፌዴራሉና የሚመለከታቸው የክልል አመራሮች እና ወንድማማች ህዝቦች በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ፣  በኦሮሚያና በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ ተፈጥረው የነበሩትን ችግሮች በመፍታት ረገድ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በተካሄደው እንቅስቃሴ አበረታች ሥራዎች ቢከናወኑም አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ መሃል ግን ለዘመናት አብረው የኖሩትን የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊ ወንድማማች ህዝቦችን ፈጽሞ ሊወክል የማይችል ግጭት ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ለወገኖቻችን ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በዚህ ግጭት ሳቢያ ህይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይመኛል፡፡

ችግሩ ወደከፋ አደጋ እንዳይሸጋገር ለመቆጣጠር ሲባል የአገር መከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊቶቻችን ግጭቱ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ከክልሎቹ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በትብብር በመሥራት ሁኔታውን በመቆጣጠር እና በማረጋጋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ግጭቱን በማነሳሳትና በማባባስ የተሳተፉ ወገኖችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በሚከናወነው የቁጥጥር ስራም በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም አስቀድሞ ለመከላከል ሲባል የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች በሥፍራው ተገኝተው ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ ናቸው፡፡ በግጭቱ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በጊዜያዊ ማረፊያ ቦታዎች በማቆየት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ በመደረግ ላይ ሲሆን በቀጣይም ወደቀድሞ መኖሪያ አካባቢዎቻቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ የሚደረግ ይሆናል፡፡

ችግሩን ከማረጋጋት ባለፈ በዘላቂነት ይፈታ ዘንድ መንግስት ከክልሎቹ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ህዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ከአሁን በፊት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በጊዜያዊ ግጭት ሳይረበሹ ችግሩን በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ አግባብ ለዘለቄታው ለመፍታት ሲያካሂዱት የነበረውን ጥረት አጠናክረው በመቀጠል ለችግሩ ዘላቂ ዕልባት በመስጠት ላይ አተኩረው እንዲሰሩ መንግስት ጥሪውን ያቀርብላቸዋል፡፡ የአገራችንን ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና የማይወዱ አንዳንድ ኃይሎች ጊዜያዊ ግጭቶችን በመቆስቆስና በማፋፋም አገራችንን ወደ ጥፋትና ውድመት ለመክተት እያደረጉት ያለው ማንኛውም እንቅስቃሴ ከሕዝቦቻችን ዕይታ የተሰወረ ባለመሆኑ የአገራችንን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ስትጫወቱት የነበረውን የመሪነት ሚና አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉም መንግሥት ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የአንዱ ወይም የሌላኛው ሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል፣ በሶሻል ሚዲያና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች አማካኝነት ችግሩን በማራገብና በማጋነን፣ በሽብር እና የጥላቻ ቅስቀሳ እኩይ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ አካላት ሁሉ ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ መንግሥት ያስጠነቅቃል። አንዳንድ አካላትም፣ በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር በመደናገጥ በደመ ነፍስ እየሰጡት ያለው መረጃ እና እርስ በርስ የመወነጃጀል ተግባር ችግሩን ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ከዚህ መሰሉ አድራጎት እንዲታቀቡ መንግስት ማሳሰብ ይወዳል፡፡ በዚህ መሰሉ ተግባር ላይ መሳተፍ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ከባድ ወንጀል እንደሆነም መንግሥት ማስገንዘብ ይወዳል፡፡