ኡጋንዳ ነዳጇን ለመጠቀም ለአውስትራሊያ ኩባንያ የነዳጅ ፍለጋ ፍቃድ ሠጠች

ኡጋንዳ በከርሰ ምድሯ የሚገኘውን ነዳጅ አውጥታ ለመጠቀም እንዲያስችላት አርምአወር ኢነርጂ ለተሰኘ የአውስታራሊያ ኩባኒያ የነዳጅ ፍለጋ ፈቃድ ሰጥታለች፡፡

ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ከ6 ነጥብ አምስት ቢሊዮን በርሜል በላይ ያለተጠቀመችበት የነዳጅ ሃብት እንዳላትም ተጠቅሷል፡፡

ኡጋንዳ አልበርቲን በተሰኘው የሃገሪቱ አካባቢ ይገኛል የተባለውን ድፍድፍ ነዳጅ ፈልጎ እንዲያወጣላት ነው ከአውስትራሊያው ግዙፍ ኩባንያ ጋር ከስምምነት የደረሰችው፡፡

የሃገሪቱ የኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት ኢሬኔ ሙሎኒ ስምምነቱን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነዳጁን እንዲፈልግ ፈቃድ የተሰጠው አርምአወር የኡጋንዳን ነዳጅ እና ጋዝ ተቋም ስራ በእጅጉ እንደሚያግዝ እምነት ተጥሎበታል ብለዋል፡፡

ይህ ስምምነት የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በሃገሪቱ የሚገኘውን የነዳጅ ሃብት አውጥቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የያዘውን እቅድ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ያሳያል እንደ ሙሎኒ ገለጻ፡፡

ስምምነቱ የካኒዋታባ ስምምነት የሚል ሲያሜ የተሰጠው ሲሆን ኩባኒያው ነዳጁን ፈልጎ የማውጣትና ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል ተያያዥ ስራዎችን የመስራት ሃላፊነት አለበትም ተብሏል፡፡

የነዳጅ ፍለጋ ስራው 344 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በሚሸፍን መሬት ላይ እንደሚከናወን የጠቀሱት ሚንስትሯ አጠቃላይ ስራው በሁለት ክፍሎች ተከፍሎ በቀጣዮቹ አራት አመታት ውስጥ ይከናወናልም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮና በግንባታ ወቅት ሊከሰት የሚችልን የመሬት መንቀጥቀጥ አስቀድሞ የሚጠቁም ቴክኖሎጂን የመጠቀም ግዴታም አለበት ኩባንያው፡፡

ይህን ስራ በጥንቃቄ የሚከታተል ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን አባላቱም ከሃገሪቱ የነዳጅ ባለስልጣን እና ከመንግስት ተወካዮች እንደተውጣጡም ተጠቅሷል፡፡

የነዳጅ ፍለጋ ስራው በስምምነቱ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን መከታተል፣ ለስራው የተያዘው በጀት በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን መቆጣጠርና  መሰል ተግባራት በኮሚቴው የሚከናወኑ ይሆናልም ተብሏል፡፡

በመጀመሪያው ክፍል ለሚከናወነው የነዳጅ ፍለጋ ስራ ከሚከፈለው የዘጠኝ መቶ ዘጠና ሺህ ዶላር ክፍያ ውስጥ ለስራው ማስጀመሪያ እንዲሆን የ316 ሺህ ዶላር ክፍያ መከናወኑንም ሚንስትሯ ጠቁመዋል፡፡

ኩባኒያው ከነዳጅ ፍለጋ ስራው ጎን ለጎን ኡጋንዳዊያንን የማሰልጠንና እና የማብቃት ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን ለዚህም ተጨማሪ ክፍያ ከኡጋንዳ መንግስት ይከፈለዋል ሲል ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቦታል፡፡