ለቅማንት ህዝብ የማንነትና አስተዳደር ጥያቄ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ውጤት በጣቢያዎች ይፋ እየተደረገ ነው

ለቅማንት ህዝብ የማንነት እና የአስተዳደር ጥያቄ መልስ ለመስጠት ትላንት የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ውጤት በየምርጫ ጣቢያዎቹ ይፋ እየተደረገ ነው፡፡

በዛሬው እለት ድምፅ በተሰጠባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ ቆጠራ ውጤት መለጠፉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ቦርዱ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳው መሰረት የድምፅ ቆጠራ ውጤቱ ተጠናቆ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚላክ እና ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም  አስታውቋል።

የህዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት፣ ህዝቡ በነፃነት ያሻውን የመረጠበት እና ሰላማዊ ድባብ የሰፈነበት እንደነበረም ቦርድ ገልጿል።

ህዝበ ውሳኔው በተካሄድባቸው አራት ወረዳዎች በሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች እና 24 ምርጫ ጣቢያዎች ለመምረጥ ከተመዘገቡ 23 ሺህ 283 መራጮች ውስጥ ከ89 በመቶ በላይ የሚሆኑ መራጮች ድምፅ እንደሰጡም ከቦርዱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ከደቡብ፣ ኦሮሚያ ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎች የተመረጡ ሲሆን ነባሩን አስተዳደር እና የቅማንትን ህዝብ የሚወክሉ ታዛቢዎችም በየምርጫ ጣቢያዎች ተመድበው ምርጫውን መታዘባቸው ይታወቃል።

ህዝበ ውሳኔው የጎንደር ከተማን ጨምሮ ፣ ጭልጋ፣ መተማ እና ቋራ ወረዳዎችን ያካተተ እንደነበር አይዘነጋም።