ኬንያ በናይሮቢ ዋና ዋና የንግድ ሥፍራዎች ሚኒባሶች እንዳይንቅሳቀሱ ልታግድ ነው

ኬንያ ከፊታችን እሮብ ጀምሮ በመዲናዋ ናይሮቢ ዋና ዋና የንግድ ሥፍራዎች ላይ ሚኒባስ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያግድ ህግ አውጥታለች፡፡

በናይሮቢ የንግድ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ታክሲዎችን ጨምሮ ከመጪው እሮብ አንስቶ መንቀሳቀስ አይፈቀድላቸውም ነው የተባለው፡፡

የናይሮቢ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎችን ቁጥር በመቀነስ  በከተማዋ በስፋት የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ጋብ ለማድረግ በማሰብ ነው ይህን ህግ ለማውጣት የተገደደው፡፡

ይህ አዲስ ህግ ከቀናት በኋላ ተግባራዊ ሲሆን በከተማዋ ከሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች መካከል ከሰላሳ ሺህ በላይ የሚሆኑት መንቀሳቀስ አይፈቀድላቸውም፡፡

የከተማው አስተዳደር እቅዱ ተሳክቶ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎችን ከእንቅስቃሴ ውጭ ማድረግ ከቻለ የትራፊክ መጨናነቁን ችግር ሊቀርፈው እንደሚችልም እምነት ተጥሎበታል፡፡

የናይሮቢ መንገድና ትራንስፖርት መስሪያ ቤት ኃላፊ ፍሬደሪክ ካራንጃ እንደገለጹት ለትራፊክ በናይሮቢ የሚስተዋለው የትራፊክ መጨናነቅ እልባት በሚያገኝበት መንገድ ላይ ስንሰራ ቆይተናል፡፡

የትራፊክ መጨናነቁ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የሚሄድ በመሆኑ ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ አስቸጋሪ እየሆነ ከመምጣቱም ባሻገር በስራ መግቢያ ሰዓት ላይ በስራ ገበታቸው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር እየተመናመነ ነውም ብለዋል ካራንጃ፡፡

በከተማዋ አሁን የሚስተዋለው የትራፊክ መጨናነቅ ካልተቀረፈና በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ህይወት በናይሮቢ ከባድ ስለሚሆን መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል እንደ ካራንጃ ገለጻ፡፡

ለትራፊክ መጨናነቅ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ደግሞ ተሽከርካሪዎች በመሆናቸው የተሸከርካሪዎችን ቁጥር መቀነሱ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ሆኖ አግኝተነዋል ነው ያሉት ሃላፊው፡፡

ከመጪው መስከረም ሃያ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውም ይሄው ነው ብለዋል ካራንጃ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፡፡

የናይሮቢ ከተማ አስተዳደር ከ30 ሺህ በላይ ሚኒባስ ተሸከርካሪዎችን ከእንቅስቃሴ ዉጭ ቢያደርግም በምትኩ ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ማዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡

እነዚህ ተሸከርካሪዎች ከተዘጋጀላቸው ፌርማታዎች በስተቀር መቆም፣ መጫንና ማውረድ የማይፈቀድላቸው ሲሆን በፌርማታዎች ላይም ከአምስት ደቂቃዎች በላይ መቆምም አይችሉም ነው የተባለው፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ነዋሪዎች እነዚህን ተሸከርካሪዎች መጠቀም እንዲችሉ መነሻና መድረሻቸውን የሚገልጹ መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል ሲል የዘገበው ዴይሊ ኔሽን ነው፡፡