የኖርዌይ ልዑልና ልዕልት በሚቀጥለው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

የኖርዌይ ልዑል ሀከን እና ልዕልት ሚት ሜሪት ከፊታችን ጥቅምት 27-30 በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማካሄድ እንደሚመጡ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

መሪዎቹ ይህን ጉብኝት ሲያካሂዱ በአፍሪካ ከጋና ቀጥሎ ሁለተኛው ሲሆን በኢትዮጵያ እና በኖርዌይ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ይረዳል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ተናግረዋል፡፡

ልዑል ሀከንና ልዕልት ሚት ሜሪት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ኖርዌይ ለኢትዮጵያ የልማት አጋር ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ባለፈው አመት ብቻ የ47 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጋለች፡፡

በተያዘው አመትም 1ነጥብ74 ቢሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገባችው ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ጋር በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፤ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስቀረትና በሌሎች የልማት ሥራዎች በትብብር  በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡

ስለሆነም የአሁኑ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር እና መሪዎችም በጋራ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ እንዲሰሩ የሚያበረታታ ይሆናል ሲሉ ቃል አቀባዩ በመደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ አብራርተዋል፡፡