ህገ-መንግስታዊ መብቶች እንዲከበሩ ከህዝቡ ጋር እንደሚሰራ ኦህዴድ አስታወቀ

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ በህገመንግስቱ የተቀመጡ የዜጎች መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ ከክልሉ ህዝብ ጋር በመስራት የድርሻውን እንደሚወጣ አስታወቀ።

በአዳማ ከተማ ሲካሔድ የቆየው የኦህዴድ ሰባተኛ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ዛሬ ተጠናቋል።

ኦህዴድ በክልሉ የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር ህዝቡን በማሳተፍ ከመሠረቱ በመፍታት የዜጎች ሰብዓዊ፣ዴሞክራሲያዊና ህገመንግስታዊ መብቶች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ እንዲጠበቁ እንደሚሰራ አመልክቷል።

ህዝቡ ለሚያነሳቸው ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት ከመሪ ድርጅቱ ጋር በመቀናጀት የመፍትሔው አካል ሆኖ እንዲሰራም ጠይቋል።

ድርጅቱ የደረሰበትን የትግል ደረጃ የሚያሳይ እና ወደ ቀጣይ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር 10 ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅድ ተነድፎ ወደ ተግባር መገባቱም በኮንፈረንሱ አመልክቷል።

በአመለካከት ፣በኪራይ ሰብሳቢነትና በህገወጥነት ላይ የተጀመረውን ትግል በማጠናከር የተገኘውን ድል የበለጠ ለማሳደግ ህዝቡን በዙሪያው በማሰባሰብ ርብርብ እንደሚያደርግ በኮንፈረንሱ ከድምዳሜ ላይ ተደርሷል።

ድርጅቱ ባወጣው የአቋም መግለጫም ህገወጦችና ኪራይ ሰብሳቢዎች የሸረቡትን ሴራ ለመበጣጠስና በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እንደሚሰራም አረጋግጧል።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የህዝቡን ተሳትፎ ከፍ በማድረግና በጥልቅ ተሃድሶ የተቀመጡትን የትኩረት አቅጣጫዎች በመተግበር በክልሉ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ የአቋም መግለጫው አመልክቷል። 

ትምህርት ወሳኝ የለውጥ መሳሪያ እንደመሆኑ ተተኪው ትውልድ ተረጋግቶ እንዳይማር የሚያደርጉትን የአፍራሽ ኃይሎች እንቅስቃሴ ለማምከን ወጣቱ ሙሉ ትኩረቱን በትምህርቱ ላይ እንዲያደርግ ጠይቋል።  

በአዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠሩትን ግጭቶች ሽፋን በማድረግ አፍራሽ ኃይሎች ህገወጦችና ኮንትሮባንዲስቶች በፈጠሩት እንቅስቃሴ የዜጎች መፈናቀል እና ጉዳት መድረሱን የጠቀሰው መግለጫው ድርጊቱ የህዝቦች አብሮነት ያሰጋቸው ሃይሎች ሴራ መሆኑንም አመልክቷል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ኦህዴድ በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው በዚህም የተጀመረውን የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ጠቁሟል።(ኢዜአ)