ግብጽ ከፈረንሳይ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

ግብጽ  ከፈረንሳይ ጋር ያለትን ወታደራዊ ትብብር የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች ።  

ፈረንሳይም ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻ ለግብጽ አሥራ ሁለት ያህል የአራተኛው ትውልድ  ዘመናዊ የጦር ጀቶችን ልትሸጥላት ስለመሆኑ አስታውቃለች፡፡

ግብጽ እና ፈረንሳይ በወታደራዊ ጉዳይ ሲተባበሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ፡፡ እኤአ በ 2015 ላይ ሀገሪቱ ከፈረንሳይ 24 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ተስማምታ 11 የሚሆኑትን በዚህ አመት ተረክባለች፡፡

የአሁኑ ስምምነት በከፍተኛ ባለስልጣናቱ እና በጦር መኮንኖች ማረጋገጫ ባይሰጥበትም አረብ ኒውስ የዜና ምንጭ መረጃው ደርሶኛል ሲል ዘግቧል፡፡

ፕሬዝዳንት አብዱላሂ አል ሲሲ ባለፈው ሳምንት ፓሪስን ሲጎበኙ  የፈረንሳዩ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ሚንስትር ቡርኖ ላማሪ አዳዲስ ስምምነቶች ሊኖሩ ይችላሉ እናያቸዋለን ማለታቸው በራሱ የሚያመላክተው ነገር አለ ነው ያለው አረብ ኒውስ በዘገባው፡፡

5.2 ቢሊየን ዩሮ ዋጋ አለው የተባለው ወታደራዊ ስምምነት የዋስትና ደብዳቤው ለፈረንሳዩ ኢንቨስትመንት ባንክ ተልኳል፡፡.

የዋስትና ደብዳቤ ለፈረንሳዩ ኢንቨስትመንት ባንክ ቢደርስም ግብጽ በብድር ለምትገዛቸው እነዚህ የጦር ጀቶች የመክፈል አቅሟ አጠያያቂ ነው ያሉ የፈረንሳይ ፖለቲከኞች እና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በርክተዋል፡፡

የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ሚንስትሩ ቡርኖ ላማሪ አዳዲስ ለሚሸጧቸው የጦር ጀቶች ግብጽ መክፈል የማትችል ከሆነ ስምምነቱ ለምን አይሰረዝም ተብለው ግብጽ ለ12 የጦር ጀት የሚሆን ገንዘብ ታጣለች ብለን አናስብም በማለት ምላሽ ሰጥትዋል፡፡

ፈረንሳይ ያላት ዘመናዊ የጦር አቅም ግብጽን በእጅጉ ያማለላት ስለመሆኑ ባለፉት ጥቂት አመታት የጦር አቅሟን ለማጠናከር  ከፈረንሳይ የገዛቻቸው የጦር መሳሪያዎች ማሳያ ተደርገዋል፡፡

ከ2014 እስከ 2016 ብቻ ግብጽ ከፈረንሳይ ለገዛቻቸው የጦር መሳሪያዎች 6ነጥብ 83 ቢሊየን ዩሮ ወጭ አድርጋለች፡፡ ጡረተኛው የግብጽ አየር ኃይል አባል ጀነራል ሀሺም አል ሃላቢ አሁን በናስር ወታደራዊ ትምህረት ቤት ያስተምራሉ፡፡

ፈረንሳይ ለግብጽ ባለፉት ሶስት አመታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ  የሸጠችው ሁለቱ ሀገራት ወዳጅነታቸው እያየለ በመምጣቱ ብቻ አይደለም ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ያላት ፍላጎት  ፈረንሳይ የዘመናዊ ጦር መሳሪያ እንደምታመርት ሌሎች ሀገራት እንዲያ ውቁላት በማለምም ነው ብለዋል ጀነራሉ፡፡

ፈረንሳይ እነዚህን የአራተኛው ትውልድ ዘመናዊ የጦር ጀቶች ቁጥራቸው 36 የሚሆኑትን  ለህንድ  ለመሸጥ እያሰበች ሲሆን  ከ አውሮፓዊያኑ 2009 ጀምሮ ደግሞ ለተባበሩት አረብ ኢምሬት 60 የጦር ጀቶች ለመሸጥ እየተደራደረች ነው ።