ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት ግጭቶችን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው -ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት በአገሪቱ የሚያጋጥሙትን  ግጭቶችን ለመፍታት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ ።

ጠቅላይ  ሚንስትር  ኃለማሪያም  በወቅታዊ  ጉዳዮች  ላይ  በሠጡት መግለጫ  እንደገለጹት  ምክር ቤቱ በአገሪቱ  የሚከሰቱ  የሰላምና መረጋጋት ችግሮችን በአግባቡ  ለመፍታት ህዝቡን በዋናነት በማሳተፍ ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ እና ይህም ተከታታይ የህዝብ ውይይቶችን እንደሚያጠቃልል ነው ያነሱት። 

በመግለጫቸው  የፌደራል እና የክልል የፀጥታ አካላት በተቀናጀ ሁኔታ ያለአግባብ መጠቀም የሚፈልፈጉ የጸረ ሰላም  አካላትን ከዚህ ድርጊታቸው ለማስቆም እና በዘላቂነት ይህን ድርጊት ለማጥፋት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ስራ መጀመሩን አንስተዋል።

በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ፥ በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ግብረሃይል ተቋቁሞ በቀናት ውስጥ ስራውን ይጀምራል ብለዋል።

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአንዳን አካባቢዎች  ተከስተው  የነበሩት ግጭቶች ቆመው  ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ እና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ከተፈጠረ በኋላ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እና አጋር ድርጅቶች መካከል መስማማቶች የሉም ልዩነቶች ይሰታዋላሉ የሚል ጥያቄ  የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየታየ ያለው ችግር በፓርቲዎች መካከል ሳይሆን አመራሩ ላይ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የትኛውም አካባቢ ያለ ህዝብ የእኔ ህዝብ ነው ብሎ ያለማሰብ የአቋም ችግር አለ መሆኑንና  ይህም ችግር በኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውስጥ የተስተዋለ እንደሆነ ጠቁመዋል ።

በሌላ በኩል የፀጥታ አካላት ማስከበር ያለባቸውን ህገመንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ሆኖ ሳለ ጥቂት የፀጥታ አካላት በደም እና በጎሳ ለይቶ ህዝብን የማየት አዝማሚያ እንደተስተዋለባቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አንዳንድ የፀጥታ አካላት በግጭት ውስጥ ተሳትፈው በመገኘታቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል።

 ሰላምን በማደፍረስ ተግባር  ላይ  የተገኙትን አካላት ተጠያቂ ማድረጉ ተከታታይ ስራን እንደሚጠይቅም ነው የገለፁት።

በኢህአዴግ ውስጥ ይፋ ስለማይደረግ እንጂ ቀድሞም የሀሳብ ትግል መኖሩን በመናገር፥ ሁሌም ግን ያሸነፈው ሀሳብ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ሆኖም መረጃን ከመስጠት አንፃር በመንግስት በኩል ያለው ችግር ህዝቡን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለሚናፈስ አሉባልታና የሓሰት ፕሮፖጋንዳ እንዳጋለጠው አምነዋል።

“የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በመካከላቸው ልዩነት ይታያል” ለሚለው ጥያቄም፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ አባል ድርጅቶቹ ያደረጉት ኮንፍረንስን በማሳያነት በማቅረብ “የተለያየ ፓርቲ እንዴት በተለያየ ኮንፍረንስ ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ያንፀባርቃል?” በሚለው ጥያቄያቸው መልስ ሰጥተዋል።

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክልሎች ከፌደራል መንግስቱ ይልቅ ጠንክረው እየወጡ ነው፤ ይህ እንዴት ይታያል?” በሚል ለቀረበው ጥያቄ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ይህ ደስታችን ነው የሚል ሆኗል። ህገ መንግስቱ ይክልሎችን እና የፌደራል መንግስትን ስልጣንን ለይቶ ያስቀመጠ መሆኑን ገልፀዋል።

በፌደራል መንግስቱ ድጎማ የሚንቀሳቀሱት ክልሎች በሚፈለገው ደረጃ ጠንክረው አልወጡም ባይ ናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በአጎራባች ክልሎች መካከል እየተካሄደ ያለው የህዝብ ለህዝብ ኮንፍረንስም በክልሎች ብቻ ሳይሆን በፌደራል መንግስት እቅድ ውስጥም ነበረ ብለዋል።

በኦሮሞ እና አማራ ህዝቦች መካከል የተጀመረው ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህ በቀጣይ በሁሉም ተጎራባች ክልሎች መካከል እንደሚቀጥል እና ይህም በመጨረሻ ወደ ሀገር አቀፍ ኮንፍረንስነት እንደሚመጣ ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ኢህአዴግ በነበሩትን የተሃድሶ ሂደቶች ሲያስታውሱ፥ ጥገኛው ባለሃብት በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ተጣብቆ የመበልፀግ ፍላጎት የታየበትን አካሄድ ለማረም የታለፈባቸው መሆኑን አንስተዋል።

አሁን ላይ ግን የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጥቅሙን ለማስከበር ህዝብን ከህዝብ እስከማጋጨት ደርሷል ነው ያሉት። ለዚህም በቅርቡ አወዳይ ላይ የነበረውን ሁኔታ በምሳሌነት አንስተዋል።

በዚህ አካባቢ ላይ የነበረው ግጭት መነሻ ቦታው ጫት በዋነኝነት የሚመረትበት እንደመሆኑ መጠን፥ ከዚህ ምርት አምራቹ እንዳይጠቀም መፈለጋቸው ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ ምንም እንኳ ኢኮኖሚው ቢያድግም አብሮት ያረገዘው ችግር አለ በማለት ይህም ችግር ኪራይ ሰብሳቢነት መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የበላይነቱን እስከሚያረጋግጥ ድረስ ኢህአዴግ የጀመረውን በጥልቀት የመታደስ ሂደት እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

በሳዑዲ አረቢያ ከሙስና ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ካዋለቻቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቢሊየነር የሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲንን በተመለከተ መንግስት በዲፕሎማሲያዊ መልኩ ጉዳዩን አስመልክቶ መረጃን እየተከታተለ መሆኑን ጠቅላይ  ሚኒስትሩ አያይዘው ገልጸዋል ።

ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ባለው የእሳቸው ኢንቨስትመንት ላይ እክል ይፈጠራል ብሎ መንግስት እንደማያምንም ነው የገለፁት።

ከዚህ ውጭ ግን ሳዑዲ አረቢያ ሉዓላዊ ሀገር እንደመሆኗ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሌላ ሊሰራ የሚችል ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል።