የኤርትራ ስደተኞች የሻዕቢያ መንግሥት እየፈጸመ ያለውን አፈና በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

በሰሜን ኢትዮጵያ የስደተኛ መጠሊያ ጣቢያዎች የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች የሻዕቢያ መንግስት በዜጎቹ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግድያና አፈና እንዲያቆም በመቃወም ሰልፍ ወጡ፡፡

በየመጠለያ ጣቢያቸው ሰልፍ ያካሄዱት ከ30 ሺህ በላይ ኤርትራውያ ስደተኞች በትግራይ ክልል ማይ ዓይኒ፣ ሕጻጽ፣ ዓዲ ሕርሽና ሽመልባ በሚባሉ የስደተኛ መጠልያ ጣቢያዎች የሚገኙ ናቸው።

ስደተኞቹ የሻዕቢያ መንግስት በዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን አፈናና ግድያ እንዲያቆም ጠይቀዋል።

በተለይ ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም በ28 እስልምና ሃይማኖት ተከታይ በሆኑ ኤርትራዊያን ላይ የፈጸመውን የግድያ ወንጀል አውግዘዋል።

በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖት መካከል ልዩነትና ግጭት ለመፍጠር የሻዕቢያ መንግስት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴንም እንዲያቆም ስደተኞቹ  ባካሄዱት ሰልፍ ላይ ጠይቀዋል።

ሰልፈኞቹ ካሰሟቸው መፈክሮች መካከል" በግዴታ የሚደረግ ወታደራዊ ስልጠና ይቁም!፣ የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ለአንድ ዓመት ማራዘሙን እንደግፋለን!፣ የአፍሪካ ሕብረት በኤርትራ እየተፈፀመ ያለውን ሰብአዊ ጥሰት በትኩረት እንዲመለከተው እንጠይቃለን!" የሚሉት ይገኙበቿዋል።