የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመፍጠር እገዛ እንዳደረገ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል መከበር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን  የብዝሃነት ጥያቄ  በመመለስ በህብረ ብሔራዊነት ላይ የመሠረት አንድነት እንዲፈጥሩ  እገዛ ማድረጉን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ያለው ገለጹ።        

ለ10 ዓመት ያህል  የብሔር ብሔረሰቦች በዓላት  በተከበሩባቸው  አካባቢዎችም ዘላቂነት ያላቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተጠቁሟል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መዲና ሰመራ የሚከበረውን 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሱያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት የፀደቀበት ህዳር 29 ቀን "የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን" ተብሎ መከበር ከጀመረበት ከ 1999 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በተለያዩ ክልሎች እየተከበረ ነው።

በዚህም ባለፉት ስርዓቶች የዜጎች የፖለቲካ ትኩሳትና ትልቅ ጥያቄ የነበረው ብዝኃነትን የማስተናገድ ችግር በዚህ ሕገ መንግስት አስተማማኝ ምላሽ አግኝቷል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ያለው አባተ በዚህ ወቅት እንዳሉት ህዳር 29 ቀን በ1987 ዓ.ም የጸደቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የብሔሮች የጭቆና ዘመን አብቅቶ በመላ አገሪቱ እኩልነት እንዲሰፍን አድርጓል።

መከበር ከጀመረ 11ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ አንድነትና መፈቃቀርን ፈጥሯል ብለዋል።

በእኩልነትና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ የብሔር ብሔረሰቦች አንድነት እንዲፈጠር የማይተካ ሚና እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።

በዓሉ የህዝብ ለህዝብ ትስስር መፍጠር ላይ አሁንም የሚቀሩ ስራዎች ቢኖሩም ለዜጎች ሰላም፣ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ልማት መደላድል ፈጥሯል ብለዋል አፈ ጉባኤ ያለው አባተ።

በአንዳንድ አካባቢዎች ብቅ ጥልቅ የሚሉ ግጭቶች የጥቂት ጸረ ሰላም ሃይሎች እኩይ ተግባር እንጂ የሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ሲከበር የተገኙ ተወካዮች የሚያስተላልፉት መልዕክትም ለሰላማቸው ዘብ መቆምና አንድነታቸውን ለማጠናከር ቃል እንደሚገቡ ነው ብለዋል።

ለበዓል ዝግጀት ብቻ ተብለው ጥራት በጎደለው መልኩ የተሰሩ የመሰረተ ልማት አውታሮች እንደነበሩ ገልጸው፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ዘላቂና ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ መፍጠር አንዱ የበዓሉ ግብ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ለበዓሉ ተብለው የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችም ለክልሉ የልማትና ኢንቨስትመንት ዘላቂ እድገት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።

በክልሉ በተያዘላቸው ፍጥነትና ጥራት የተሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ምናልባትም ክልሉን ካሁን በፊት በዓሉን ካስተናገዱ ክልሎች ግንባር ቀደም ሳያደርገው እንዳልቀረ ጠቁመዋል።

የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል "በሕገ መንግስታችን የደመቀ ሕብረ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።(ኤዜአ)