የፀጥታው ምክር ቤት በሱዳን አብዩ የተሠማራውን የሰላም አስከባሪ ኃይል ቆይታን አራዘመ

የፀጥታው ምክር ቤት  በሱዳን አብዬ የተሰማራው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ኃይልን ተልዕኮ ለስድስት ወራት በድጋሚ አራዘም፡፡
ምክር ቤቱ በቀጠናው የተሰማራውን ሰላም አስከባሪ ኃይል ቁጥርም እስከ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 2018 ሚያዚያ ወር ድረስ ወደ 4ሺህ 791 ለማሳደግ ማቀዱም ተገልጿል፡፡ 

በሱዳን አብዬ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሀይል የተቋቋመው የሱዳን መንግስትና የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጪ ግንባር በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የምትገኘውን የአብዬ ግዛት የይገባኛል ጥያቄ ካቀረቡበት ጊዜ አንስቶ በአካባቢው የድንበር ማካለል ስራ እንዲሰራ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ከተፈራረሙና የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል አካባቢውን እንዲቆጣጠር ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ነበር፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት ባሳለፈነው ረቡዕ ባስተላለፈው ውሳኔ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ድንበር ላይ በምትገኘውና ሁለቱን ሀገራት ውዝግበ ውስጥ በከተተችው አብዬ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማሩ የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ግዳጃቸው እስከ ፈረንጆቹ 2018 ግንቦት ወር ድረስ እንዲራዘም ወስኗል፡፡

15ቱ አባል ሀገራትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል በ2011 በቀጠናው ሰላምን ለማስከበር የተፈቀደለትን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በውሳኔው በአንድ ድምጽ በመስማማት በአብዬ እየፈጸም ያለውን ተልዕኮ ለተመሳሳይ ጊዜ አራዝመዋል፡፡

ምክር ቤቱ በተመሳሳይም የሀገራቱን ድንበር ለማካለልለ እና ሂደቱን ለመከታተል በአብዬ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል የሚያደርገውን ድጋፍም  እስከ አ.አ 2018 ሚያዚያ ወር ድረስ ማራዘሙን አስታወቋል፡፡

የምክር ቤቱ 15 አባል ሀገራት የአብዬ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል  በአካባቢው ያለውን ሰላም ለማስፈን እና መረጋጋትን ለመፍጠር እያደረገ ባለው ተግባር ሁለቱ ሀገራት ከአቢዬ እና ወደ አብዬ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች  ነጻ ፤ ያልተገደቡ እና ቀላል  እንዲሆኑ የበኩላቸውን ድርሻ ካልተወጡ እና ለሰላም አስከባሪ ሀይሉ ብቻ አገልግሎትን የሚሰጡና ይፋዊ የሆኑ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ፤ ተሸከርካሪዎችን   እንዲሁም ሌሎች ግብአቶችን ለማቅረብ አስቸጋሪ የሚሆኑ ክስተቶችን ለማስወገድ ቁርጠኛ አቋም ካልያዙ ምክር ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ የመጨረሻ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም የጸጥታ ምክር ቤቱ በቀጠናው የተሰማራውን ሰላም አስከባሪ ኃይል ቁጥር እ. ኤ.አ በ2018 ሚያዚያ ወር ድረስ ወደ 4791 ለማሳደግ የወሰነ ሲሆን ይህ ቁጥር ግን ምክር ቤቱ ለአብዬ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ድጋፍ ካላደረገ ወደ 4235 ሊቀንስ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ የተልዕኮውን መራዘም በበጎ ጎኑ ቢቀበሉትም ስምምነቱን ወደ ተግባር ላይ ለመቀየር ጥረት ባለመደረጉና የድንበር ማካለሉ ስራ በታቀደለት ጊዜ ባለመካሄዱ ቅር መሰኘታቸውን ተናግረዋል ።

ተወካዩ አያይዘውም ሰላም አስከባሪ ኃይሉ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ መገልገያ መሣሪያዎች  መዘግየታቸው እና በአካባቢው እንዳይገቡ የተከለከሉ ፖሊሶች በአካባቢው መገኘታቸው  በቀጠናው ያለውን የትብብር እጦት የሚያሳዩ ምሳሌዎች ናቸው  ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን አምባሳደር አኩዌ ቦና በበኩላቸው የሰላም አስከባሪ ኃይሉን ተልዕኮ መራዘም የተቀበሉት ሲሆን ለስኬታማነቱም የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

አምባሳደር አኩዌ ይህ ውሳኔ ከግብ ሊደርስ የሚችለው  የደቡብ ሱዳን  እና የሱዳን ባለስልጣናቶች በመተባበር  በመካከላቸው ያሉ  ማንኛውም አይነት ልዩነቶችን  ለመፍታት የመፍትሄ አቅጣጫ ሲያስቀምጡና በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም  ከስምምነት ሲደርሱ  እንደሆነ  አስገንዝበው ይህን ውሳኔ ተከትሎም የአብዬ ህዝቦች ኑሮአቸው ለማቃናት እና  በቀጠናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚያበረክቱ ያላቸውን  ተስፋ ገልጸዋል፡፡ ( ምንጭ: ሱዳን ትሪቡን)