ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትና ድህነትን መዋጋት ከሚሹ አገራት ጋር ትሠራለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትና ድህነትን መዋጋት ከሚሹ አገራት ጋር መሥራት የሚያስችል ግልፅ ፖሊሲ እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ኳታር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት ጉዳይ ላይ ለመወያየት በኳታር ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል።

በቆይታቸውም ኢትዮጵያና ኳታር ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለጋራ ልማት መሥራት የሚችሉባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍንና ድህነት እንዲወገድ ከተለያዩ አገራት ጋር  በትብብር ትሰራለች።

አገሪቷ በቀጣይ ለምታከናውነው የተፈጥሮ ጋዝ ምርት በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ከሆነችው ኳታር ልምድ ለመውሰድና በቅንጅት ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል።

በሳይንስና ምርምር ሥራዎች ከዓለም ግዙፍ የምርምር ተቋማት ጋር በቅንጅት የምትሰራው ኳታር ለኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች የማስተርስና የፒ.ኤች.ዲ ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት ቃል ገብታለች ብለዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ዓለም አቀፍ እውቅና ያላት በመሆኗ ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት እንደምትፈልግ ገልፃለች።

በመሆኑም አገራቱ ለአፍሪካ፣ ለገልፍ አገሮች በአጠቃላይ ለዓለም ህዝቦች ሰላምና ደህንነት በቅንጅት በመሥራት የበኩላቸውን ሚና እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።

ለአርሶ አደሮች የማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት፣ ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ልብና የኩላሊት በሽታዎችን በመከላከልና በታዳሽ ኃይል ዙሪያ በቅንጅት ለመሥራት መስማማታቸውንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከ20 በላይ የኳታር ባለሃብቶች በምግብ ዋስትና ፣ በቱሪዝም ኢንዱስትሪና በሌሎችም የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል፡፡

"ፖሊሲያችን ሽብርተኝነትንና ድህነትን መዋጋት ከሚፈልጉ አገራት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡( ኢዜአ)