ሲንጋፖር ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ማቋረጧን ገለጸች

ሲንጋፖር  ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ማቋረጧን አስታወቀች ።  

ሲንጋፖር  ያቋረጠችው  ፒዮንግያንግ በተደጋጋሚ ባደረገችው የኒኩለር ሙከራ ከአሜሪካ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር የገባችውን እሰጣ ገባ ተከትላ ነው፡፡

ሰሜን ኮሪያ የመንግስታቱን ድርጅት ማዕቀብ ወደ ጎን በመተው በተደጋጋሚ ያደረገችውን የኒኩለር ሙከራ ተከትሎ ከዓለም ማህበረሰብ ወቀሳ እየደረሰባት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ወቀሳውን ተከትሎም አሜሪካ እና አጋሮቿ በፒዮንግያንግ ላይ የማግለል እርምጃ እየወሰዱም ይገኛሉ፡፡

የኪም ኦን ጁንግ መንግስት የሙጥኝ ያለው የኒኩለር ጦር ፕሮጀክት አገሪቱን ለኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እየዳረጋትም ይገኛል፡፡ ነገር ግን ሰሜን ኮሪያ አልበገርም ባይነቷን እያጎላች ትገኛለች፡፡

ሲንጋፖር እና ሰሜን ኮሪያ ለዓመታት በንግድ እና ኢኮኖሚ ትስስር የዳበረ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል፡፡   ለአብነት ያህል በባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት አገራቱ በነበራቸው የንግድ ልውውጥ ሲንጋፖር 8ኛ ደረጃ ያላት የሰሜን ኮሪያ የንግድ አጋር ለመሆን በቅታለች፡፡ በዚህም የሰሜን ኮሪያን ገቢ ንግድ ዜሮ ነጥብ  በመቶ ለመሸፈን ችላለች፡፡

ምንም እንኳ የፒዮንግያንግን በከፍተኛ ደረጃ የንግድ ግንኙነቱን እየመራች የምትገኘው ቻይና ብትሆንም፤ ሲንጋፖር ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ከመጣል የማይተናነስ የተባለውን የንግድ ግንኙነቷን አቋርጣለች፡፡

አገሪቱ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በጦር መሣሪያ ንግድ ከኩባ እና ሰሜን ኮሪያ ጋር የነበራት ሚስጢራዊ ግንኙነት በመንግስታቱ ድርጅት ተደርሶበት ማስጠንቀቂያ እንደተጣለባት ይታወሳል፡፡

አሁን ግን በተገላቢጦሹ ለፒዮንግያንግ ጀርባዋን የሰጠች ትመስላለች፡፡ ሲንጋፖር ቀስ በቀስ ከኪም ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧ ለፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ መገዛቷን ያሳያል እየተባለ ይገኛል፡፡( ምንጭ:ቢቢሲ)