ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ምልክት ሁኖ ይቀጥላል-መንግስት

ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የአገራችንን ህዳሴ ለማፋጠን በጋራ እየገነቡት የሚገኝ ታላቁ ፕሮጀክት መሆኑን  የኢፌዲሪ መንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

ጽሕፈትቤት ዛሬ ባወጣው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ ፤ግድቡ ተጠናቆ ወደሥራ እንዲገባ ለማስቻል ሌት ተቀን  ርብርብ በመደረግ ላይ ሲሆን መላው የሀገራችን ህዝቦች ድጋፋቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ ነው ያለው ።

የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨትም ባለፈ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ፕሮጀክታችን መሆኑን አስገንዝቧል ።

መንግስት የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነበት ዕለት ጀምሮ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል መተማመን እንዲፈጠር ለማድረግ ብዙ ርቀትን በመጓዝ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ጠቅሷል ።

የሶስትዮሽ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም ሃሣብ ከማመንጨት ጀምሮ የጥናቱን ውጤት ለመተግበር ፍፁም ተባባሪ መሆናቸውን በታችኛው ተፋሰስ  ሀገራትና በአለም አቀፍ ደረጃ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት መሆናቸውን ያረጋገጡበት መሆኑን አስታውሷል ፡፡

አሁንም  የግድቡን ግንባታ በድብብቆሽ ሳይሆን ግልጽነት በተሞላበት መልኩ በማከናወን ላይ  እንደሚገኝም ኣመልክቷል ።

የተለያዩ የተፋሰሱ አገራት ተወካዮችና የዓለም የመገናኛ ብዙሃን ግድቡን ቦታው ድረስ በመሄድ እንዲጎበኙት ያደረግነውም ከዚሁ ጋር ተያያዢነት ያለው ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ ።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እነሆ

 በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች /ቤት የተዘጋጀ

ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

ህዳር 15 ቀን 2010 .

ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ምልክት ሁኖ ይቀጥላል

ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የአገራችንን ህዳሴ ለማፋጠን በጋራ እየገነቡት የሚገኝ ታላቁ ፕሮጀክታችን ነው።

ግድቡ ተጠናቆ ወደሥራ እንዲገባ ለማስቻል ሌት ተቀን  ርብርብ በመደረግ ላይ ሲሆን መላው የሀገራችን ህዝቦች ድጋፋቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሀይል ከማመንጨትም ባለፈ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ፕሮጀክታችን ነው።

መንግስት የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነበት ዕለት ጀምሮ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል መተማመን እንዲፈጠር ለማድረግ ብዙ ርቀትን በመጓዝ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

የሶስትዮሽ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም ሃሣብ ከማመንጨት ጀምሮ የጥናቱን ውጤት ለመተግበር ፍፁም ተባባሪ መሆናችን በታችኛው ተፋሰስ  ሀገራትና በአለም አቀፍ ደረጃ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት መሆናችንን ያረጋገጥንበት ነው፡፡

አሁንም  የግድቡን ግንባታ በድብብቆሽ ሳይሆን ግልጽነት በተሞላበት መልኩ በማከናወን ላይ እንገኛለን።

የተለያዩ የተፋሰሱ አገራት ተወካዮችና የዓለም የመገናኛ ብዙሃን ግድቡን ቦታው ድረስ በመሄድ እንዲጎበኙት ያደረግነውም ከዚሁ ጋር ተያያዢነት ያለው ጉዳይ ነው።

የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነበት ዕለት ጀምሮ መንግስት ከታችኛ የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት እና ውይይት አስቀምጦት የነበረውን መርህ ሳይሸራርፍ በመተግበር ላይ ይገኛል።የግድቡ ግንባታ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ እንደማይኖረውም ሲገልጽ ቆይቷል።  ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ ተግባራትን እና ሰነዶችን አቅርቧል።

መተማመንም እንዲፈጠር ለማድረግ በራሱ ተነሳሽነት ተጽእኖው በአለም አቀፍ ሞያተኞች እንዲጠና እስከመፍቀድ ደርሷል።

ድህነትን በመዋጋት የሀገራችንን ልማት ማፋጠን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሞት የሽረት ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። ይህንን የሞት ሽረት ጉዳይ አሸንፎ ለመውጣት ለሚደረገው ትግል ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው።

ከግብርና መር ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምናደርገው ሽግግር ዋነኛው እና ወሳኙን ሚና ሊጫወት የሚችለው ጉዳይ በቂ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ መሆኑ ይታወቃል።ለዚህም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድባችን በሁሉም ኢትዮጵያውያን የነቃ ተሳትፎ እውን ወደ መሆን ተቃርቧል።