“መልካም አስተዳደር ልማት እና ዴሞክራሲን ለማስፈን ይረዳል” ጠቅላይ ሚኒስትር

መልካም አስተዳደር ለመዋቅራዊ ሽግግር፣ ልማት እና ዴሞክራሲን ለማስፈን እንደሚረዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ ።

የ2017 የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ፤ መልካም አስተዳደር መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት፣ ለእድገትና ዴሞክራሲን ለማስፈን እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።

አፍሪካ ቀጣይ ጉዞዋን በራሷ መወሰንና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማስመዝገብ የምትችልበት እድል እንዳላትም አንስተዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ላሚን ሞሞዱ ማኔህ በበኩላቸው፤ አህጉሪቱ የረጅም ጊዜ የሽግግር ሂደቷን ላማሳካት በፖለቲካዊ፣

ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን መፍታት አለባት ብለዋል።

በአህጉሩቱ ያለውን ርሃብ ለማስወገድም መልካም አስተዳደር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።

መድረኩ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በሚያስችሉ መንገዶችና በመንግስት ፖሊሲዎች ላይ ውይይት ይደረግበታል።

ከዚህ ባለፈም የአፍሪካ ሃገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ያስመዘገቧቸው መዋቅራዊ የሽግግር ለውጦች የሚታይበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

መልካም አስተዳደር ለመዋቅራዊ ሽግግር በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የተዘጋጀው ጉባኤ እስከ መጭው ረቡዕ ይካሄዳል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።