ዶክተር ወርቅነህ ከሶማሊያና አልጀሪያ አቻዎቻቸው ጋር ተወያይተዋል

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሶማሊያና አልጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በአፍሪካ ህብረት 30ኛው ጉባኤ ጎን ለጎን ተወያይተዋል።

ዶ/ር ወርቅነህ ከሶማሊያ አቻቸው አህመድ ኢሳ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ትኩረት ትሰጣለች።

የአገራቱን ትስስር ከሰላምና ደህንነት ባሻገር በኢኮኖሚና በህዝብ ለህዝብ ረገድ ማሳደግ እንደሚገባ ዶ/ር ወርቅነህ ተናግረዋል።

ለቀጠናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የአካባቢው አገራት ተቀራርቦ መስራት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ኢሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ለምታበረክተው ገንቢ ሚና እምነት አለን ብለዋል።

በኢጋድ ጥላ ስር ለሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን ኢትዮጵያ እያበረከተች ያለውን አስተዋፅኦም አድንቀዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች የኢትዮ-ሶማሊያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ከአንድ ወር በኋላ በሞቃድሾ ለማካሄድ ተስማምተዋል። የአገራቱን ዲፕሎማሲያ ግንኙነት ለማሳደግም ሁለቱ ሚኒስትሮች ተስማምተዋል።

ዶ/ር ወርቅነህ ከአልጀሪያ አቻቸው ሜሳህል አብዱልቃድር ጋርም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ሁለቱ አገራት ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን ስትራቴጅካዊ አጋር መሆናቸውን ዶ/ር ወርቅነህ ገልጸዋል።

አገራቱ ከሁለትዮሽ ግነኙነት ባለፈ የአፍሪካን ጥቅሞች በሚያስከብሩ አጀንዳዎች ላይ ተባብረው ለመስራት ተስማምተዋል።ምንጭ-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር