ቱርክ በሶሪያ ኩርዶች በሰነዘረችው ጥቃት ቢያንስ 260ዎቹን መግደሏን አስታወቀች

ቱርክ ለአራት ቀናት በሶሪያ የኩርድ ተዋጊዎች እና የእስላማዊ መንግስት ታጣቂዎች ላይ በሰነዘረችው ጥቃት ቢያንስ 260ዎቹን መግደሏ ይፋ ሆነ፡፡

ጥቃቱ ትኩረቱን ያደረገው በሰሜን ሶሪያ ኩርዶች የተቆጣጠሩት የአፍሪን ግዛት ላይ መሆኑንም የቱርክ መከላከያ አስታውቋል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎም አሜሪካ እና ሩሲያን ጨምሮ ሃያላኑ መንግስታት ተቃውሟቸውን በአንካራ ላይ በማሰማት ላይ ናቸው፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቱርኩ አቻቸው ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር በጉዳዩ ላይ የስልክ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቡድኑ በዋሽንግተን የሚደገፍ ነውና  አንካራ የአፍሪን ግዛቱን የኩርዲሽ YPG ሓይል መደምሰሷ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣንን በመጥቀስ ሮይተርስ ፅፏል፡፡

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ያደረግነው ከአሜሪካ፣ ሩሲያ እና የሶሪያ መንግስታት ጋር የመጋጨት ዓላማ ኖሮን ሳይሆን ቱርክ ደህንነቷን ለማስጠበቅ ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ለማመላከት ነው ሲል የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጉዳዩን እረፍት የሚነሳ ነው በማለት ገልጸውታል፡፡

በዘርፈ ብዙ የውስጥ ችግሮች የተጠመደች ሶሪያ በተለይም ደግሞ አይኤስ እንደልብ ይመላለስባታል በሚትባለው የሰሜን ምስራቅ ሶሪያ የአፍሪን ግዛት ላይ አሜሪካ ከበሽር አላሳድ ቁጥጥርም በላይ የሆነውን የኩርዲሽ YPG ሓይል በመደገፍ የእስላማዊ መንግስት ሚሊሻዎቹን ከቀጠናው ማስወገድ የዋሽንግተን አብይ ዓላማ ነው፡፡

አሜሪካ እና ሩሲያ በሶሪያ የሚደግፉ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች አሏቸው፡፡ ከዚህ የተነሳም ሞስኮ እና ዋሽንግተን አንካራን ለተግባሯ አበጀሽ ይሏታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

እንዳውም አንድ የፕሬዚዳንት ትራምፕን ከፍተኛ ባለስልጣን በምንጭነት ተጠቀምኩ ብሎ ሮይተርስ እንደዘገበው ዋሽንግተን አንካራ በሶሪያ ኩርዶች ላይ የወሰደችውን ጥቃት እንደ ጦርነት መቀስቀሻ ምልክት ትመለከተዋለች ይላል፡፡

አለመግባባቶቹ እንዲረግቡ ግን ኤርዶሃን ከትራምፕ ጋር በጉዳዩ ለመነጋገር ቀጠሮ ስለመያዛቸው ከአሜሪካ ባለስልጣናትም ሆነ ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ቢሆኑ የቱርክ ወታደራዊ ሀይል በአፍራን ግዛት ጣልቃ በመግባት ወታደራዊ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ ጉዳዩን በቅርበት መከታተል እንደሚፈልጉ ለቱርክ አቻቸው ኤርዶሃን ነግረዋቸዋል ተብሏል፡፡

ከክሬምሊን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ደግሞ ቭላድሚር ፑቲን ከቱርክ አቻቸው ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ጋር በስልክ ሲያወሩ የአንካራው ኦፕሬሽን የሶሪያን ድንበር መረጋጋት የሚነሳ እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የጣሰ ነው ሲሉ ወቅሷቸዋል ነው የተባለው፡፡

የክሬሚሊኑ ቤተመንግስት መረጃ እንዳመላከተው ሁለቱ መሪዎች በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ እና ለሶሪያ ቀውስም መፍትሄ ለማምጣት በሰላም እንደሚደራደሩ አስቀምጠዋል፡፡

ሩሲያ በሶሪያ ያሉትን ተቃዋሚዎች በመቃረን የፕሬዚዳንት በሺር አላሳድ ቁልፍ ደጋፊ በመሆን መሰለፏ ይታወቃል፡፡

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶጊሊ የአንካራ ፍላጎት ዋሽንግተን የሶሪያ ኩርዲሽ YPG ቡድንን መደገፍ እንዲታቆም ብቻ ነው ሲሉ የመንግስታቸውን አቋም አስተጋብተዋል፡፡

የቱርክ መንግስት ቃል አቀባይ ኢብራሂም ካሊን አንካራ በሶሪያ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የሚታቆመው ቁጥራቸው ከ3 ነጥብ 5 በላይ የሆነው በቱርክ የሚኖሩ የሶሪያ ስደተኞች በሰላም በቀያቸው መመለስ ሲችሉ ነው ብሏል፡፡

አሜሪካ በበኩሏ በሰሜን ሶሪያ ከትሞ የቆውን የ YPG ቡድን እንደ የዲፕሎማሲ ጡንቻዋ ተጠቅማ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሪነት የሶሪያን የእርሰ በእርስ ጦርነት ለማብቃት በጄነቫ ለመካሄድ ለታቀደው ድርድር እንደ መሳሪያ ለመጠቀም ትሻለች፡፡

የአንካራ እና ዋሽንግተን ግንኙነት የሚወሰነው በአሜሪካ ቀጣይ እርምጃዎች ነው ይላሉ የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶጉሊ፡፡

በኔቶ ከፍተኛ ቁጥር የያዘውን የወታደራዊ ሀይል በማበርከት በ2ኛ ደረጃ የተቀመጠችው አንካራ በአየር እና ምድር በወሰደቻቸው ጥቃት በርካታ ህይወትን ቀጥፋለች፡፡

በሶሪያ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ዘገባ እንዳመላከተው የቱርክ የአፍሪን የአየር ጥቃት የ23 ንፁሃን ህይወትን ቀጥፎ ሺዎችን ደግሞ አፈናቅሏል፡፡

የሶሪያ መንግስት ወታደሮች ደግሞ ጥቃቱን በመሸሽ ላይ ያሉትን ዜጎች ወደ አሌፖ እንዳይገቡ በመከልከል ላይ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቱርኩ ጥቃት በትንሹ 5 ሺህ ዜጎችን አፈናቅሎ 50 ሺህ የሚደርሱትን ለእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ማድረጉን የአካባቢው ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ጂም ማቲስ አይ ኤስን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ገደል የሚከት ነው አሉ፡፡

የነጩ ቤት ቃልአቀባይ ሳራ ሳንደርስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኤርዶሃን ጋር በሚያደርጉት ንግግር ቱርክ አደጋዎችን እንዴት መቀነስ እንዳለባት ሊያነሱ ይገባል ሲሉ ተደመጡ፡፡

አንካራ ግን የቱርኩን ኩርዲሽ ይህ በአሜሪካ የሚደገፈው የሶሪያ ኩርዲሽ እንዳይገነጥልባት ትሰጋለችና አካሄዱ ከጂሃዲስቱ አይ ኤስም በላይ ሰላም እንደሚነሳት ታስገነዝባለች፡፡