ምክርቤቱ ወይዘሮ ሳሚያ ዘካሪያ የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ አድርጎ ሾመ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የሚመሩ ዘጠኝ የስራ አመራር አባላትን ሹመት ተቀብሎ አፀደቀ።

በሁለት ተቃውሞና ሁለት ድምፀ ተአቅቦ የጸደቀው ሹመቱ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ሰባት የቦርድ አባላትን ያካተተ ነው።

ወይዘሮ ሳሚያ ዘካሪያ የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ፤ አቶ ደሞዜ ማሜን ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተሹመዋል።

ቀሲስ በላይ መኮንን፣ ወይዘሮ የሺሀረግ ዳምጤ፣ ፕሮፌሰር ፈቴን አባይ፣ ወይዘሮ ፀሃይ መንክር፣ አቶ ተካልኝ ገብረስላሴ፣ አቶ ጀማል መሃመድና አቶ ሃብቴ ፍቻላ የቦርዱ አባላት ናቸው።

ለቦርዱ ስራ አስፈፃሚነት ከተመረጡት አባላት መካከል አራቱ ሴቶች ሲሆኑ ከአጠቃላይ አባላቱ የሴቶች ምጣኔው 44 በመቶ መሆኑን ምክር ቤቱ መልካም ብሎታል።

በቦርዱ ሰብሳቢነት የተሾሙት ወይዘሮ ሳሚያ ዘካሪያ በሰጡት አስተያየት የምርጫ ቦርዱን ተግባር ከማከናወን አንፃር በአገሪቱ ነፃ የምርጫ ስርዓት ለማስፈን እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ከወገንተኝነት ነጻ በሆነ፣ በፍትሃዊነትና ለህገ-መንግስቱ በመታመን ስራቸውን ለመወጣት እንደሚተጉም ገልፀዋል።

ወይዘሮ ሳሚያ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። (ኢዜአ)