የንግዱን ዘርፍ ችግሮች ለመፍታት ባለሃብቶች ከመንግስት ጋር እንዲሰሩ ተጠየቀ

የንግዱን ዘርፍ ችግሮች ለመፍታት ባለሃብቶች ከመንግስት ጋር እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ማምሻውን በንግዱ ዘርፍ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ የንግዱ ማህበረሰብ ወኪል ከሆነው ከንግድ ዘርፍ ማህበራትና ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች ባለቤቶች የዘርፉ ፈተናዎች ተብለው በቀረቡ ጥያቄዎች ነው የተጀመረው።

የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና አጠቃቀም፣ የገንዘብ አቅርቦት፣ የመንግስት ተቋማት የአገልግሎትና ሎጅስቲክስ ችግር፣ ሙስና፣ ያልተገባ ውድድር፣ ህገ ወጥ ንግድና በጸጥታና ደህንነት ችግር የትራንስፖርት መቆራረጥ ከፈተናዎቹ መካከል ተጠቅሰዋል።

የትኩረት ማጣት፣ ፍትሃዊነት አለመኖር፣ የመሬት አቅርቦትና በንግዱ ውስጥ የመንግስት እጅ መግባትም ትኩረት ይሻሉ የተባሉ ናቸው።

ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በርካቶቹ ችግሮች የሁሉንም የጋራ ጥረትና ትብብር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በመንግስት በኩል በቅርቡ በሂደት በሚከናወኑ የሪፎርም ስራዎች እየተመለሱ እንደሚሄዱም ገልፀዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ካልተገቡ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብና ለዘላቂም ሆነ ለጊዜያዊ መፍትሄው ከመንግስት ጋር እንዲሰራም አሳስበዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት በቀላሉ የሚፈታ አለመሆኑን ጠቅሰው እንደ ጊዜያዊ መፍትሄ ያለውን ከብክነት በጸዳ መልኩ መጠቀም፣ በውጭ ካሉ ኢትዮጵያዊያን የሚላከውን ማበረታታት፣ ጥቁር ገበያን ማስቀረት፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገኙ የግብርና ምርቶች ላይ በአግባቡ መስራት ይገባል ብለዋል።