በደቡብ ክልል በህዝቦች መካከል ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለማጠናከር እርምጃዎች ተወስደዋል -አቶ ደሴ ዳልኬ 

በደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በህዝቦች መካከል ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ተግባራትና እርምጃዎች መወሰዳቸውን  የደቡብ ክልል  ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደሴ ዳልኬ ገለጹ ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  በዛሬው ዕለት በሐዋሳ ስታዲየም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት መድረክ ላይ  ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በደቡብ ክልል  ብዝሃነትን  በመጠበቅ በህዝቦች መካከል ዴሞክራሲያዊ አንድነት  ማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ አቋሞች ተወስደዋል ፣ ተግባራትም ተከናውነዋል ።

ብዙሃነት በአግባቡ ከተያዘ ውበት  መሆኑንና በጋራ ለማደግ እንዲሁም ለለውጥ በማምጣት ወደ  ብልጽግና ለማምራት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ያሉት አቶ ደሴ የክልሉ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለማጠናከር  የወሰዱት እርምጃዎች ለአገር አንድነት ያላቸውን አቋም የሚያመላክት ነው ብለዋል ።

የደቡብ ክልል ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለሰላም ፣ለልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦ  በአገሪቱ ሰላም ፣ አንድነትና ዕድገት እንዲመዘገብ ካላቸው ቁርጠኝነት በመነሳት መሆኑን አቶ ደሴ አመልክተዋል ።

በደቡብ ክልል የህዝቦችን  ተጠቃሚነትን የሚጎዱ ሙሰናና  ብልሹ አሠራሮችን አገልግሎት መጓደልን ለመቅረፍ  የተለያዩ ሥራዎችን ቢሠሩም የተፈለገውን ያህል  ውጤት አላመጡም  ብለዋል አቶ ደሴ ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን ዕድገት፣አንድነትና የዴሞክራሲያዊ ግንባታ ሂደትን አስተማማኝ መሠረት ላይ ለመጣል ለሚያደርጉት ጥረትም የደቡብ ክልል  ከጎናቸው በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል ።

 በመጨረሻም አቶ ደሴ  ዳልኬ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ  መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው  በደቡብ ክልል አስተዳደር ስም ምኞታቸውን ገልጸዋል ።