በዓለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ

ከፈረንጆቹ 2014 ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

በአለም ሀገራት መካከል እየተነሱ ያሉ የተለያዩ ውዝግቦች ለነዳጅ ዋጋው መናር ምክኒያት ተደርገው ተጠቅሷል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 በዓለማችን ሀያላን ሀገራት እና በኢራን መካከል ከተደረሰው የኒውክሌር ስምምነት ሀገራቸውን አስወጣለው ማለታቸውን ተከትሎ በአሜሪካና በኢራን መካከል ውዝግቡ በርትቷል፡፡

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሩሃኒ አሜሪካ ከኢራን ጋር ከተደረሰው የኒኩሌር ስምምነት የምትወጣ ከሆነ ሀገራቸው የምትወስደው የአጸፋ ምላሽ ከባድ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ 

ይህ ውዝግብ ደግሞ ለነዳጅ ዋጋ መናር እንደ ቀዳሚ ምክንያት ነው የተወሰደው፡፡

ከፈረንጆቹ 2014 ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ  ጭማሪ ያሳየ ሲሆን አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በ75 የአሜሪካን ዶላር እየተሸጠም ይገኛል፡፡

ይህም ከፈረንጆቹ 2014 ወዲህ በነዳጅ ዋጋ ላይ የተመዘገበ ከፍተኛው ጭማሪ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው የተከሰተው ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የጀመረችው የኒውክሌር ድርድር ተገቢ ያልሆነ መሆኑን በመግለጽ ሀገራቸው በአለማችን ሶስተኛ ከፍተኛ ነዳጅ አምራች በሆነችው ኢራን ላይ ሌሎች ማዕቀቦችን ለመጣል ማሰቧን የሚያመላክት ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአሜሪካና በሶሪያ መካከል የተቀሰቀሰው አለመግባባት ለነዳጅ ዋጋው መናር እንደምክንያትነት መነሳቱን ዘገባው አመላክቷል፡፡

የነዳጅ ዋጋ ከያዝነው የፈረንጆቹ አመት የካቲት ወር ጀምሮ በሀያ በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ካሳለፍነው አመት ሰኔ ወር ከተመዘገበው ዝቅተኛ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ70 ከመቶ ጭማሪ ነው ያሳየው፡፡

ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያትነት የተጠቀሰው የነዳጅ ላኪ ሀገራት ህብረት ኦፔክ እና ሩሲያ በጋራ ያካሂዱት የነበረው የነዳጅ ምርት መቋረጡን ተከትሎ የነዳጅ ፍላጎቱ በመጨመሩ ነው፡፡

የነዳጅ ላኪ ሀገራት ህብረት እና ከህብረቱ ውጪ የሆኑ ሀገራት በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2017 ህዳር ወር በኦስትሪያ ቬና ባደረጉት ስብሰባ እሰከ አ.አ 2018 መጨረሻ ድረስ  በቀን ለአለም ገበያ አቅርበውት የነበረውን የ1.8 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ ምርት ለማቋረጥ ከስምምነት መድረሳቸውን ያስታወሰው ዘገባው ይህን ስምምነትም የነዳጅ ላኪ ሀገራት ህብረት ባሳለፍነው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ ባካሄዱት ስብሰባ ዳግም አረጋግጠውታል፡፡

ስምምነቱ እስከ ፈረንጆቹ ታህሳስ ወር 2018 ተግባራዊ እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን የነዳጅ ላኪ ሀገራት ህብረት አባል ሀገራት በመጪው የፈረንጆቹ ሰኔ ወር በሚያደርጉት ስብሰባ ስምምነቱ በአለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ እንደሚገመግሙ ይጠበቃል ሲል ኢንቨስትመን ዊክ ዘግቧል ፡፡

በአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ኢራንን በተመለከተ ባደረጉት ውይይት  የኢራንን የኒውክሌር ትብብር ለማስጠበቅ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳይቷል ነው የተባለው፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸውን ከ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት   ለማስወጣት ወይም በአዲስ ስምምነት ለመተካት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለግንቦት አራት ቀነ ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል፡፡ (ሲጂቲኤን)