የአዲስ አበባ ምክር ቤት የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ጉባኤውን አጠናቀቀ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ላለፉት አራት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን  2ኛው መደበኛ ጉባኤውን የተለያዩ ሹመቶችን በመስጠት ዛሬ ጉባኤውን አጠናቋል፡፡

በዚህም መሰረት አቶ እንደሻው ጣሰው የትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣ ሺሰማ ገብረስላሴ የከተማ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ሃርጋሞ ሀማሞ የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ መሰፉን አበራ የንግድ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተመዋል፡፡

በተጨማሪም ወ/ሮ አረጋሽ ቸኮል የከተማ ልማት እና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች  ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ወ/ሮ ፈቲያ መሀመድ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ተሸመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፌጉባኤ አቶ ተስፋዬ ተርፋሳ ምክር ቤቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአፈፃፀም መጓተት በታየባቸው ዘርፎች የሚሰራቸው ስራዎች ተጠናክረው እንድቀጥል እና የህብረተሰቡን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጠዋል ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ የተለያዩ አዋጆችን ያጸደቀ ሲሆን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን የሠራተኛ መተዳደሪያና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ስለመከታተል የቀረበ አዋጅ፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ በተመለከተ የቀረቡ አዋጆች ከፀደቁት አዋጆች መካከል ይገኛሉ፡፡

በምክር ቤቱ የፀደቁ አዋጆችም የአሰራር ቅልጥፍና በማምጣት እና አዳዲስ መስሪያ ቤቶችን ለማቋቋም የሚያስችል እንደሆነም አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የተሰጡ ሹመቶችም የተጓደሉ የኃላፊነት ቦታዎችን ለማሟላት ሲሆን ሹመት የተሰጣቸውም  ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ኢንዲወጡ አሳስበዋል፡፡