3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በጋምቤላ ክልል ተጀመረ

ግንቦት 24/2013(ዋልታ) – 3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በጋምቤላ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በተገኙበት ተጀምሯል፡፡

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “እንደባለፉት ዓመታት ሁሉ ነዋሪዎቻችንን አስተባብረን በመስራት ጋምቤላን ብሎም ሀገሪቱን አረንጓዴ የማድረግ ግባችንን አጠናክረን የምናስቀጥልበት ነው ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከሀገራችን አልፎ ጎረቤት ሀገሮች ጭምር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እቅድ መያዙን ጠቅሰው ሀገሪቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ቀጠናዊ ህብረት ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት ማሳ ነው፡፡

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን ሊያበረክት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል በበኩላቸው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሀገር አቀፍ ዕቅድ ውስጥ 4.8 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ቦታ ለክልሉ የተሰጠ ቢሆንም ከዕቅዱ በላይ 6.5 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በምክር ቤቱ አዳራሽ የተካሄደ ሲሆን በነገው ዕለት በመንገሺ ወረዳ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በይፋ እንደሚጀመር ከጋምቤላ ፕረስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡