የአገሪቱን ስላም ለመጠበቅ ህብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል- መንግስት

የአገሪቱን  ሰላም ለማስጠበቅና የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ወደ ኋላ እንዳይመለስ  ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም  የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ ፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በሳምንታዊ  መግለጫው መንግስት በተለያዩ ቦታዎች የታዩትን ግጭቶች በቁጥጥር ስር ለማዋልና ወንጀለኞቹንም ለፍርድ ለማቅረብ በፅናት እንደሚሰራ ገልጿል፡፡

የመግለጫው ሙሉ መልእክት  የሚከተለው ነው፡

ከመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ  ሳምንታዊ የመንግስት አቋም መግለጫ

የሰው ልጅ በተፈጥሮ ከመኖር የሚቀድም አላማ የለውም ፡፡ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ፤ ወልዶ ለመሳም፤ ዘርቶ ለመቃም  እና የህይወትን በረከቶች በሙሉ ለማጣጣም ፤ ሰላም መተኪያ የሌለው ብርቱ መሳሪያ ነው ፡፡ አገራችን  ኢትዮጵያ ፤ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት እያጋጠሟት የነበሩትን ቀውሶች እና ህዝቧን ስጋት ላይ ጥለው የነበሩት ግጭቶች ተወግደው ሁሉም ዜጋ በሰላም መኖር ይችል ዘንድ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል ፡፡

የመንግስት ፣ የህዝብና የወዳጆቻችን ጥረትና ምኞት ፍሬ አፍርቶ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በመላ አገራችን ሊያሰኝ በሚችል መልኩ አንጻራዊ ሰላም ፣ አየር መንፈስ በመጀመሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡

በአገራችን ውስጥ እያከናወንናቸው ያሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎችና በውጭ አገርም ያስመዘገብናቸው ዲፕሎማሲያዊ ድሎች የዚሁ ሰላምና መረጋጋታችን ውጤቶች ናቸው ፡፡

አሁን ላለንበት ነባራዊ ሁኔታ እንድንበቃና በተሻለ አገራዊ ቁመና ላይ እንድንገኝም ዋናው ተዋናይ የሃገራችን ህዝብ ነው ፡፡

መንግስትም ህዝቡን በማሳተፍና ያለመታከት በመስራት የዜጋውን ጥያቄ ለመመለስ በፍጹም ቁርጠኝነት መንፈስ በመስራት ላይ ይገኛል ፡፡ ይኸው ትግል ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች ፤ ጥረት ውጤቶቻችንን ከማጨናገፍና ሩጫችንን ከማደናቀፍ ውጪ፤ ለማንም ምንም የሚበጁ አይደሉም ፡፡  ከነዚህ የነውጥ ድርጊቶችም የሚያተርፍ አንድም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ በፍፁም አይኖርም ፡፡

በመሆኑም፤ መንግስት ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ እንደገለፀው ፣ የጋራ ቤታችን ለሆነችው ለዚች አገር ፤  የሚበጀውን ሁሉ ለማድረግ የሚረባረበውና ወደፊትም በጀመርነው ልክና መጠን ብቻ ሳይሆን ፤ እያደር በመጠናከርም ጭምር ፤ የለውጥ ተግባሩን የሚያስኬደው ፤ ህዝቡንና ህዝቡን በመተማመን ብቻ እንደሆነ እሙን ነው ፡፡

ያለ ሰላም እስከየትም መጓዝ አንችልም ፡፡ ያለ ሰላም የምናስበው ብልፅግናና እድገት ፤ ለውጥና ታላቅነት ፤ ፍቅርና ማህበረሰባዊ ልህቀት በአገራችን ሊሰፍኑ አይችሉም ፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ፤ ለሰላሙና ለሃገራዊ አንድነቱ ዘብ የመቆም ፤ ሃገራዊና ሞራላዊ ግዴታ አለበት ፡፡

መንግስት፤ በተለያዩ ቦታዎች የታዩትን ግጭቶች በቁጥጥር ስር ለማዋልና ወንጀለኞቹንም ለፍርድ ለማቅረብ በፅናት ይሰራል ፡፡

በቀጣይም፤ የህግ የበላይነትንና የአገራችንን ሰላም ለማስጠበቅ መንግስት ከሚሰራው ጎን ለጎን ህዝባችንም የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ወደ ኋላ እንዳይመለስ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል ፡፡

በመጨረሻም፤ የትኛውም  ዜጋ ጥያቄ ቢኖረው ከመንግስት ጋር ተንጋግሮ ችግሮቹን ለመፍታት በመንግስት በኩል ዝግጁነቱ እንዳለ ለመግለፅ ይወዳል ፡፡

ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት