አየር መንገዱ በያዝነው ወር ወደ ባርሴሎና ከተማ በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰኔ 24፣ 2010 ዓ.ም በስፔኗ የባርሴሎና ከተማ በረራ እንደሚጀምር አስታውቋል።

ወደ ከተማዋ የሚደረገው በረራ በቦይንግ በ787-800 ድሪምላይነር አውሮፕላን መሆኑን አየር መንገዱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የባርሴሎና ከተማ የአየር መንገዱ 13ኛ የአውሮፓ መዳረሻ ከተማ እንደሆነና በከተማዋ የሚደረገው በረራ የአየር መንገዱ ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ የሆነው ራዕይ 2025 የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን የማስፋት እቅድ አካል እንደሆነም አስረድተዋል።

ወደ ባርሴሎና የሚደረገው በረራ አዲስ አበባን ማዕከል በማድረግ በባርሴሎና ከተማ የሚገኙ የንግድ ሰዎችና ቱሪስቶች አየር መንገዱ ካለው 58 የአፍሪካ መዳረሻዎች ጋር እንዲተሳሰር የሚያደርግ መሆኑንም አመልክተዋል።

ባርሴሎና በአውሮፓ ትልቅ የሚባሉ የንግድ ትርኢቶችና አውድ ርዕዮች ከሚቀርቡባቸው ከተሞች ከሆላንድ አምስተርዳም ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ  በአሁኑ ወቅት  በአምስት አህጉሮች 110 መዳረሻዎች አሉት። (አዜአ)