አሜሪካ በመስቀል አደባባይ የደረሰውን የቦንብ ጥቃት ለማጣራት የኤፍቢአይ ባለሙያዎችን ትልካለች

ባለፈው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ የተካሄደው ሰላማዊ ሰለፍ ላይ የደረሰውን የቦንብ ጥቃት ለማጣራት አሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ( ኤፍቢአይ) የምርመራ  ቡድን አባላትን በመላክ ድጋፍ እንደምታደርግ  የአሜሪካ ምክትል የንግድ ሚንስትር ጊልበርት ካፕላን ገለጹ ።

በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካ ምክትል የንግድ ሚንስትሩ ከኢፌደሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ወይይት ባደረጉበት ወቅት ባለፈው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የደረሰውን የቦንብ ጥቃት የአሜሪካ  መንግሥት  በጥብቅ እንደሚያወግዘው ተናግረዋል ።

ምክትል ሚንስትሩ ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲያዊ ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል ።

ኢትዮጵያ በፖለቲካው ዘርፍ  ከአሜሪካ  ጋር ባላት ግንኙነት  ውጤት ያስመዘገበች መሆኑንና  ይህ ውጤት በኢኮኖሚውም  ሊደገም እንደሚገባ  በውይይቱ ተጠቅሷል ።

ምክትል ሚንስትሩ የአሜሪካ  ስመጥር  ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋለነዋያቸውን  የማፍሰስ  ፍላጎት  እንዳላቸውን  በውይይቱ ተናግረዋል ።

ዶክተር  ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው  በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭና ዕድልን  የአሜሪካ  ኩባንያዎች  አንዲቀጠሙበት  ጥሪ  አቅርበዋል ።

በኢትዮጵያ  ያለው ዕድገት ፣ አንጻራዊ ሰላም ለአሜሪካ  ኩባንያዎች መዋለነዋያቸውን እንዲያፈሱ  ምቹ  ሁኔታ  የሚፈጥረ በመሆኑ  በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች  እንዲሠማሩ ጋብዘዋል ።

የአሜሪካ  ኩባንያዎች በተለያዩ  የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሠማርተው  ችግሮችም ካጋጠሟቸው  በጋራ  ለመፍታት  ኢትዮጵያ  ዝግጁ  ስለመሆኗ  ዶክተር  ወርቅነህ  ተናግረዋል ።

የሁለቱ አገራት የንግድ ግንኙነት  ማሻሻያ  ሰነድ ይጸድቃል  ተብሎ እንደሚጠበቅ  ተገልጿል ።