ከተማ አስተዳደሩ በቦንብ ፍንዳታ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የ10 ሚሊዮን ብር ደጋፍ አደረገ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ቅዳሜ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተደረገው የድጋፍና የምስጋና ሰልፍ ላይ በቦንብ ፍንዳታ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የ10 ሚሊዮን ብር ደጋፍ አደረገ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከተማ አስተዳደሩ ኮሚቴ በማቋቋም ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች መረጃ በማጣራት ተገቢው ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚያመቻች ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና አመራራቸው ላመጡት ለውጥ የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ  ተጎጂዎችን ለመርዳት የተደረገው ርብርብ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

በቦንብ ፍንዳታው የሁለት ሰዎች ህይዎት ማለፉንና 156 በሚሆኑት ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

ለጥፋቱ ተጠያቂ የሚሆኑትን መንግስት አጣርቶ ለህዝብ እንደሚያሳውቅና ጠንከር ያለ እርምጃም እንደሚወስድ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከተጎጂዎች እንደማይርቅና የከተማዋ ነዋሪዎችም ሆነ መላው ኢትዮጵያውያን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በቀጣይ ህብረተሰቡ ድጋፍ ማድረግ የሚችልበትን የባንክ ህሳብ ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፋ አንደሚያደርግ የገለጹት ከንቲባው እስከዛው ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልጉ አካላት እስከ ከንቲባው ጽህፈት ቤት ድረስ በመምጣት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡