በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ላይ የሚካሄደው ምርመራ ተጀምሯል

በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ላይ የሚካሄደው ምርመራ ተጀምሯል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘይኑ ጀማል የምርመራውን ሂደት አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በምርመራ ሂደቱ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ የተውጣጡና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን አስረድተዋል።

በምርመራው የአሜሪካ ብሄራዊ የምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) ባለሙያዎች ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ምርመራው የድርጊቱን ፈጻሚ? የድርጊቱን ኢላማ? በድርጊቱ ውስጥ የፖሊስ ተሳትፎ መኖር አለመኖሩን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለመ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በምርመራው ሂደት ውስጥ የአይን እማኞች፣ ተጎጂዎች እንዲሁም ተጠርጣሪ ግለሰቦች የመረጃ ምንጭ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፥ በቅዳሜው ሰልፍ ላይ የታየው ክፍተት ሆን ተብሎ በፖሊስ ቸልተኝነት የተፈጠረ መሆን አለመሆኑም ይታያል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎ የተፈጸመውን ጥቃት ማክሸፍ አለመቻሉ በእለቱ የተስተዋለ ክፍተት መሆኑን አውስተዋል።

ከዚህ ባለፈም በእለቱ በመድረኩና በህዝቡ መካከል ያለው ርቀት መስፋት ሲገባው መቀራረቡም እንደ ክፍተት ተወስዷል ነው ያሉት።

ድርጊቱ ከመድረኩ ባልራቀ ቦታ ላይ መፈጸሙም በእለቱ እንደ ክፍተት የታየ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ቦምብን ያክል መሳሪያ ብዙ ህዝብ በተሳተፈበት ሁኔታ መገኘቱ በፌደራል ፖሊስ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ የተጀመረውን የምርመራ ውጤትም ከስር ከስር ለህዝቡ ለማድረስ እንደሚሰራ በመግለጫቸው አንስተዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም አመራሮችን እና የፍተሻ አስተባባሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።(ኤፍቢሲ)