”አገር ወዳዱ የአፋር ህዝብ የአገሪቷን ዳር ድንበር ያስጠበቀ ጀግና ህዝብ ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

”አገር ወዳዱ የአፋር ህዝብ  የአገሪቷን ዳር ድንበር ያስጠበቀ ጀግና ህዝብ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፋር ክልል የሥራ ጉብኝት ለማድረግና ከህዝቡ ጋር ለመወያየት ዛሬ ሰመራ ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድረን ጨምሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀግናና ኩሩ በሆነው የአፋር ህዝብ መካከል መገኘታቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።

”የሰው ዘር መገኛ እምብርት የሆነችው አፋር ህዝቦች ‘እንኳን እኛ ግመሎቻችን ዳር ድንበሯን ያውቁታል’፤ አፋርን ከኢትዮጵያ ኢትዮጵያን ከአፋር ውጭ ማሰብ የማይታሰብ ነው” ብለዋል።

ክልሉ ከታደለው የተፈጥሮ መስህቦች አንዱ የሆነውን የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም የመስኖ ልማቱን ማፋጠን እንደሚገባም ተናግረዋል።

”የአፋር ህዝብ አስቸጋሪውን የተፈጥሮ ሁኔታ ተጋፍጦ በጥበብ በማከም በረሃውን ወደ በረከትነት የለወጠ ህዝብ ነው” ያሉት ዶክተር አብይ፤ የቤት አሰራር ጥበቡ፣ ዳጉ የተባለ የመረጃ ልውውጥ ባህሉና የእንስሳት ሃብት አጠቃቀሙ በበረሃው ውስጥ ለመኖር የሚያስችለውን ስልት የቀየሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ሴቶችን፣ ሰላምና ፀጥታ ላይ ያለው ፍርድ አሠጣጥ፣ እንግዳ ተቀባይነት የሚመስሉትን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ብሔሮች ብሔረሰቦችን ተቀብሎ በጋራ የሚኖር ህዝብ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ለክልሉ መሰረተ ልማት መጎልበት መንግስት ቁርጠኛ ሆኖ እንደሚሠራ ጠቁመው፤ ለአብነትም አዋሽ ወንዝን ተጠቅሞ የልማት ተግባራትን እንደሚያከናውን አስረድተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሃጂ ስዩም አወል እንደተናገሩት፤ ክልሉ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሥራዎች ለውጥ አምጥቷል። በአሁኑ ወቅትም የህዝቡን ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመለስ እየተሰራ ነው።

የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ለክልሉ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው  ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሰኔ 16 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመጡትን ለውጥ ለመደገፍ በወጣው ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘው፤ በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡና ለተጎዱ ወገኖች ቤተሰቦች መጽናናትና ብርታት ተመኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በሱማሌ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ፣ በጋምቤላ ክልሎች ተዘዋውረው ከህዝብ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።(ኢዜአ)