በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ ከ40 በላይ ግለሰቦች ተያዙ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ግጭት እጃቸው አለበት በሚል የተጠረጠሩ ከ40 በላይ ግለሰቦች መያዛቸውን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።

በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ከሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ.ም አንስቶ የተከሰተው የፀጥታ ችግር በአገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ያስተባበሩት በመሆኑ የክልሉ መንግስት የፀጥታ ችግሩን ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዛሬው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት ከሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ማምሻ አንስቶ በአሶሳ፣ በሸርቆሌና በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ በተቀሰቀሰ ግጭት የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ49 ሰዎች ላይም ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል።

የክልሉ መንግስትም በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ለጠፋው የሰው ህይወትና የአካል ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል፡፡

ችግሩ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሐይማኖት አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በመመካከር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ህዝባዊ ውይይቱ ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚካሄድ አስታውቀው የተፈጠረውን ችግር በዋናነት ያስተባበሩትና የተሳተፉት ከ40 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

“አላስፈላጊ እርምጃ በወሰዱ የፀጥታ አካላት ላይም ምርመራ ተካሂዶ እርምጃ ይወሰዳል” ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ ችግሩን በመፍታት ህደት የክልሉ ህዝብ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። (ኢዜአ)