በአንዋር መስጊድ አካባቢ የተነሳው ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ በአካባቢው ሱቆች ላይ ጉዳት አደረሰ

በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ አካባቢ በተነሳው ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት በአካባቢው የነበሩ ሱቆች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ፡፡

አደጋው ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ የተነሳ ሲሆን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ባለሥልጣን በሰዓቱ ቢደርስም ቶሎ ወደ ውስጥ ባለመግባቱና በፍጥነት እሳቱን መቆጣጠር ባለመቻሉ ንብረታቸው እንደወደመባቸው በሰዓቱ የነበሩና ተጎጂዎች ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

በመስጊዱ ላይ ምንም አደጋ ባይደርስበትም የሐይማኖት ትምህርት በሚሰጥበት ቦታ ላይ እሳቱ በከፊል ተከስቶ ቁራኖችን ማቃጠሉ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ሸሪፍ ሀሰን ከእሳት አደጋ ሰራተኞች በተጨማሪ  የአካባቢው ማህበረሰብ አደጋውን እንዳይስፋፋ ተከላክለዋል ብለዋል፡፡

የሌሎች ሐይማኖት አባቶች በቦታው በመገኘት ጉብኝት አድርገው ከጎናቸው እንደሚሆኑና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ለአደጋው ተጎጂዎች ገልጸዋል፡፡

በቃጠሎ የአካል ጉዳት ባይደርስም በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት በመድረሱ የማጣረት ስራ እየተከናወነ  ይገኛል፡፡

አደጋውን ለመቆጣጠር 112 የእሳት አደጋ ሰራተኞች እንደተሰማሩ እና 15 የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎችን እንደተጠቀመ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል መቆጣጠሪያ ባለሥልጣን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የእሳት አደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ እስከአሁን አልታወቀም፡፡