የፀረ ሽብር ህጉን ጨምሮ በፍትሕ ተቋማት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን የሚመረምር የህግና የፍትህ አማካሪ ጉባኤ ተቋቋመ

የፀረ ሽብር ህጉን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፍትሕ ተቋማት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መርምሮ ለመንግስት የሚያቀርብ የህግና የፍትህ አማካሪ ጉባኤ መቋቋሙን የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ገልጿል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ሰኔ 22 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጉባኤው 13 አባላት ያሉት ሲሆን በተለይ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ማነቆ የሆኑት አተገባበሮችን እና ህብረተሰቡ በፍትህ ተቋማት ላይ የሚያቀርባቸውን እሮሮዎችን እያጠና ለመንግስት ያቀርባል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጉባኤው በጥናት ያቀረባቸውን ችግሮች ምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ እየተከታተለ ለሶስት አመታት ያህልይቆያል፡፡

የፌደራል ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ እንዳሉት የአማካሪ ጉባኤው አባላት በትምህርት ዝግጅት፣ በስራ ልምድ እና በህይወት ተሞክሮ የተመረጡ ሲሆኑ ተቋሙ ለጥናት ከሚያውለው ወጪ ያለፈ ወርሃዊ ደመወዝ አይከፈላቸውም፡፡

‹‹ተቋሙ የህግ ማሻሻያ ብቻ ሳይሆን ለፍትህ ስርዓቱ የሚያግዙ ምክረ ሃሳቦችን ያቀርባል›› ነው ያሉት፡፡