ሚኒስቴሩ መሠረታዊ የንግድ ሸቀጦችን በአግባቡ በማያቀርቡ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

በመንግስት ድጎማ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ መሠረታዊ የንግድ ሸቀጦች በተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡ እንዳይቀርቡ በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ ።

የንግድ ሚኒስቴር በላከው መግለጫ መንግሥት ለህብረተሰቡ በድጎማ መልክ የሚያቀርባቸውን መሠረታዊ የንግድ ሸቀጦች በአግባቡ እንዲቀርቡ ለማስቻልም ህብረተሰቡና ህግ አስከባሪ አካላት የበኩላቸውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል ።   

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በስኳር፣ ፓልም የምግብ ዘይትና የዳቦ ስንዴ ላይ ክትትልና ቁጥጥር  በማድረግ  ለህብረተሰቡ እንዲዳረስ ሲሰራ መቆየቱንም በመግለጫው  ጠቁሟል ።

ሚኒስቴሩ የተለያዩ መሠረታዊ ምርቶች በተገቢዉ መንገድ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ከአምራቾች፣ አቅራቢዎች፣ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታዉቋል።

ሆኖም በከፍተኛ የመንግስት ድጎማ የሚቀርቡት መሠረታዊ ሸቀጦች በህጋዊ የአቅርቦትና ሥርጭት ሰንሰለት ለህብረተሰቡ ተደራሽ አለመሆናቸውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባደረጋቸዉ የማጣራት ሥራዎች ማረጋገጡን አስታዉቋል።

በተለይም  በዳቦ ስንዴ አቅርቦት ላይ የነበሩ ችግሮች ተፈተዉ አቅርቦቱ በአስተማማኝ ሁኔታ የቀጠለ ቢሆንም አቅርቦቱ ያልተጀመረ በማስመሰል የተለያዩ የማጭበርበር ሥራዎችን የሚሠሩ አካላት መኖራቸውንም መረጋገጡን መግለጫው አመልክቷል።

ስለዚህም ህብረተሰቡም ሆነ በየደረጃዉ የሚገኙ አስፈፃሚና የህግ አስከባሪ አካላት በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ህገወጥ ድርጊቶችን እንዲከላከልና ለህግ እንዲያቀርብ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል ። 

በተጨማሪም በተባሉት ህገ ወጥ ድርጊቶች የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ ያሳሰበዉ የንግድ ሚኒስቴር እነዚህ አካላት ከድርጊታቸዉ የማይቆጠቡ ከሆነ አስፈላጊዉን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስታዉቋል።

በመጨረሻም ህብረተሰቡ ማንኛዉንም ህገ ወጥ ድርጊት ሲያስተዉል በ8478 እና 6319 የስልክ መስመሮች በመደወል ጥቆማ እንዲሰጥም ሚኒስቴሩ ለዋልታ ቴሌቭዥን በላከዉ መግለጫዉ አስታዉቋል።