በመተማ በኩል 98 ክላሽንኮቭን ጨምሮ 3 ብሬንና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ሲገቡ ተያዙ

በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉን የገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር ሚሊሻ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አራጋው አዛናው እንደገለጹት የጦር መሳሪያው የተያዘው የነዳጅ ማመላለሻ ተሸከርካሪው ልዩ ቦታው ሆርሸዲ  ሲደርስ ባጋጠመው የመገልበጥ አደጋ ነደጁ በመደፋቱ ነው።

በዚህም 98 ክላሽን ኮቭ፣ 3 ብሬንና 1ሺህ 294 የቱርክ ሽጉጥ ከ120 የክላሽ ጥይት ጋር መያዝ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የጦር መሳሪያው የተያዘው ኮድ 3 -93875 ኢት በሆነ የነዳጅ ቦቴና በተሳቢው ውስጥ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአደጋው ቀላል ጉዳት ያጋጠመው አሽከርካሪው በመተማ ሆስፒታል ህክምና ተደርጎለት በቁጥጥር ስር መዋሉንም ኃላፊው ተናግረዋል።

ከህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ጊዜ በቦቴ መኪናዎች ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እንደሚጓጓዝ መረጃ ቢደርስም የነዳጅ ተሸከርካሪዎችን አስቁሞ ለመፈተሽ አስቸጋሪ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

ወጣቱና የአካባቢው ህብረተሰብ ከጥቆማ መሥጠት ጀምሮ በቁጥጥር ስር የዋለውን የጦር መሳሪያ ተሸክሞ ፖሊስ ጽህፈት ቤት በማድረስ በኩል ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነው መሰል የመከላከል ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 

የገንዳውኃ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ኢንስፔክተር ክንድነው አሰፋ በበኩላቸው “ይህ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ወደ መሀል አገር  ቢገባ ኖሮ  ሰላምን በማወክ ከፍተኛ ውድመት ያስከትል ነበር” ብለዋል።

የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በሚቀጥሯቸው አሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ክትትል በማድረግ ችግሩን ለመቆጣጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ተባባሪነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል፡፡

የነዳጅ ጭነት ተሸከርካሪዎች ከሱዳን ሲወጡ ተፈትሸው የሚወጡበት መንገድ በመንግስት በኩል እንዲሰራም ጠይቀው በድንበር ዋና ዋና መተላለፊያ በሮች ላይም ጥናትንና መረጃን መሰረት ያደረገ ክትትል እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በአካባቢው  ከፍተኛ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዳለ የገለጹት ኢንስፔክተር ክንድነው  በቀጣይ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የቁጥጥሩ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡(ኢዜአ)