ፈረንሳይ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደምታደርግ ገለፀች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ከፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ በፓሪስ መክረዋል፡፡

ሀገራቱ የቆየ ወደጅነታቸውን በማጠናከር ለተሻለ ለውጥ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
ሰላምና ደህንነት፣ንግድና ኢንቨስትመንት ፣ ትምህርትና ባህል ደግሞ በጋራ ለመስራት ከተስማሙባቸው ዘርፎች ይጠቀሳሉ ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሀመድና ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሁለትዮሽ ውይይታቸው በኋላ በሠጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የሀገራቱን ትብብር የበለጠ ለማሳለጥ ይሰራል፡፡
ፈረንሳይ በቅርስ ጥበቃ ያላትን አቅም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ እንድታውለው የቀረበላትን ጥሪ እንደተቀበለች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ገለፀዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የመጣውን ሰላም በማስቀጠል በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ሰላም እንዲጠናከር ለማድረግ በጋራ ለመስራት ከስምምነት መደረሱንም አስታውቀዋል፡፡ 
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አማካኝነት በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ ሀገራቸው ዠግጁ እንደሆነች ገልፀዋል፡፡

በቴሌኮም በትራንስፖርት በመሠረተ ልማት ዘርፍ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላትም ፈረንሳይ ገልጻለች።

 ከቀጠናው ሰላም ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እያደረጉ ያሉትን ተግባር እንደግፋለን እናደንቃለንም፤በተለይ በሳቸው ተነሳሽነት በኢትዮጵያና በኤርትራ የተፈጠረውን የሰላም ሂደት እንዲሳካ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል ኢማኑኤል ማክሮን ።

ከኤርትራ ከጅቡቲም ሆነ ከሌሎች የቀጠናው ሀገራት ጋር ኢትዮጵያ እየፈጠረች ያላቸውን የሰላምና የትብብር መንፈስ እንደፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን እንደ አውሮፓ ህብረት የምንደግፈው ነው ብለዋል ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፡፡

ከሁለት ወራት በኋላም የተጀመረውን ግንኙነት ለማጠናከር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም ተናግረዋል፡፡