ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት በመሆን ተመረጡ

የህዝብ ተወካዮች  ምክር ቤት  በዛሬው ዕለት  ባደረገው   5ኛው ዙር  4ኛ  የሥራ ዘመን 4ኛው  መደበኛ ጉባኤ  ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊን  የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት በማድረግ በሙሉ ድምጽ  መርጧል ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የመደበኛ ስብሰባ ላይ  ክብረት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊን እጩ የጠቅላይ  ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት  በማድረግ ለምክር ቤት  አቅርበዋል ።

ክብርት ወይዘሮ መዓዛ በህግ  የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያገኙ ሲሆን  ከአሜሪካው የኬንታኪ ዩኒቨርስቲ  በዓለም አቀፍ ግንኙነት በማስተርስ ዲግሪ መመረቃቸውን  ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል ።

ወይዘሮ መዓዛ  የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ ከመሳተፋቸውም በላይ በአገሪቱ የሴቶች  መብት እንዲከበርና የሴቶች የህግ ማህበር እንዲቋቋም ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው በምክር ቤቱ ተገልጿል ።

ወይዘሮ መዓዛ  በ1997 ምርጫ ላይ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይትን በማዘጋጀት በሚታወቀው ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ድርጅት  በዋና ዳይሬክተርነት  የመሩ ሰው መሆናቸውም በጠቅላይ ሚንስትሩ ተገልጿል ።

በአሁኑ ወቅት ወይዘሮ መዓዛ የፍትህና የህግ ማሻሻያ ኮሚቴ   ምክትል ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ መሆኑንና  ከላይ  የተጠቀሱት የትምህርት ፣ የሥራና ያካበቱት ልምድና እውቀት ለጠቅላይ  ፍርድቤት ፕሬዚዳንት እጩነት እንዲቀርቡ ያደረጋቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ገልጸዋል ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ደንብ አንቀፅ 81 ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት  በጠቅላይ  ሚንስትሩ አማካኝነት ለጠቅላይ ፍርድቤት በእጩነት ለምክር ቤቱ የቀረቡት ወይዘሮ መዓዛ  የምክር ቤቱን  ሙሉ ድምጽ በማግኘት የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚደንት ሆነው ተሾመዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ  በዛሬው ዕለት  የምክር ቤት  ስብሰባ  ለጠቅላይ ፍርድቤት ምክትል ፕሬዚደንትነት አራት እጩዎችን ለመምረጥ ጥረት  መደረጉን ጠቅሰው  ሦስቱ በተለያዩ ምክንያቶች እጩነታቸውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል ብለዋል ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንትነት በእጩነት ያቀረቡት አቶ ሰለሞን አረዳን መሆኑን ለምክር ቤቱ  ተናግረዋል ።

አቶ ሰለሞን አረዳ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በህግ ያገኙ ሲሆን ከሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ህግ፣ ህግ  እንዲሁም ሶስተኛ  ማስተርስ ዲግሪያቸውን በህዝብ አስተዳደር ከሃርቫርድ  አግኝተዋል ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደገለጹት አቶ  ሰለሞን  በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድቤትና በአገር ውስጥ በከፍተኛ ፍርድቤት ለረጅም ጊዜ የዳኝነት አገልግሎት የሠጡ እንዲሁም  የፌደሬል የመጀመሪያ  ፍርድ ቤትም ምክትል ፕሬዚደንት በመሆን ያገለገሉ ስለመሆነቸው ለምክር ቤቱ አስረድተዋል ።

ምክርቤቱም ለጠቅላይ ፍርድቤት ምክትል ፕሬዚደንትነት እጩነት የቀረቡት አቶ ሰለሞን አረዳ  ሹመትን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል ።

በመጨረሻም  ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፕሬዚደንትና በምክትል ፕሬዚደንትነት የተመረጡት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊና አቶ ሰለሞን አረዳ  የጠቅላይ ፍርድቤት ዳኛ በሆኑት አቶ አሰግድ ጋሻው አማካኝነት  ህዝባቸውን በታታሪነትና በቅንነት ለማገልገል ቃለ ማሃላ ፈጽመዋል ።