በየአመቱ 600ሺ ህጻናት በአየር ብክለት ለሞት እንደሚዳረጉ ጥናት አመላከተ

በየአመቱ 600ሺ ህጻናት በአየር ብክለት ለሞት እንደሚዳረጉ አንድ ጥናት ይፋ አደረገ፡፡

ከቤት ውስጥም ይሁን ከተለያዩ ቦታዎች የሚለቀቁት በካይ ነገሮች በየአመቱ ከ500ሺ በላይ ህጻናትን ለሞት እንደሚያጋልጥ የአለም የጤና ድርጅት ባጠናው ጥናት ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡

93 በመቶ ዕድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ 1.8 ቢሊየን ወጣቶች በተበከለ አየር ምክንያት ለከፋ ጉዳት እንደሚጋለጡም ተገልጻል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው በፈረንጆቹ 2016 ብቻ 600 ሺህ የሚሆኑ ህፃናት በአየር ብክለት ምክንያት በሚፈጠር የአተነፋፈስ ችግር ለሞት ተዳርገዋል፡፡

የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሪክተር ዶክተር ቴወድሮስ አድሀኖም የተበከለ አየር በሚሊየን የሚቆጠሩ ህፃናትን ህይወት እየቀጠፈ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ጤና ድርጅቱ መረጃ በአለም ላይ ከሚገኙ 10 ሰዎች 9ኙ የሚተነፍሱት አየር የተበከለ እንደሆነ እና በዚህም ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ ተገልጿል፡፡

በብዛት የአየር ብክለት የሚያስከትሉት ሰልፊት እና ካርበን የሚባሉት ንጥረ ነገሮች  ያለጥንቃቄ ወደ አየር በሚለቀቁበት ወቅት  በቀጥታ ወደ ሳንባና ወደ የተለያዩ የመተንፈሻ አካላት በመግባት ትልቅ የጤና ቀውስ ይፈጥራሉ፡፡

በተለይ ይህ አይነቱ ችግር የሚፈጠረው ባላደጉ ሀገራት የሚገኙ ህጻናት ላይ እንደሆነም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

የአለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው ካደጉት ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ያላደጉ ሀገራት 52 በመቶ በተበከለ አየር ተጠቂ ናቸው፡፡

ይህ የአየር ብክለት ከህጻናቱና ከሌሎች ሰዎች በተጨማሪ በዋነኛነት ለአደጋ የሚያጋልጠው ነፍሰጡር ሴቶችን ሲሆን ያለጊዜው እንዲወልዱ ያደርጋቸዋል ከዛም ባለፈ የህጻኑ ክብደት ላይ ተጽዕኖ ያመጣል ሲል ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡