ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሃመድ አብዱላሂ ጎንደር ከተማ ገቡ

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ጎንደር ከተማ ገቡ።

መሪዎቹ በአማራ ክልል ለሚያደርጉት ጉብኝት ዛሬ ጎንደር ከተማ ሲገቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በቆይታቸውም ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የጎንደር ቆይታቸውን ሲያጠናቅቁ በባህር ዳር ከተማ ጉብኝት እንደሚያደርጉም ነው የሚጠበቀው።

የመሪዎቹ ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሁለቱ መሪዎች አማራ ክልልን እንዲጎብኙ በይፋ መጋበዛቸውን ተከትሎ ነው።

ግብዣው በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ የሚገኘውን የለውጥ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ ትብብርን ለማመቻቸት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ አካል ነው ተብሏል።

መስከረም 2011 በአስመራ የተካሄደው የሶስትዮሽ ምክክር ተከታይ የሆነው ጉብኝት ውይይቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያለመ ሲሆን፥ በጎንደርና ባህር ዳር የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጉብኝትም ያካትታል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)