63 ሰዎች በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ

እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ 63 ሰዎች በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፌደራል አቃቢ ህግ አስታወቀ ።

የጠቅላይ አቃቢ ህግ ዋና አቃቢ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በዛሬው ዕለት በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት ወንጀለኛ ባልሆኑ ግለሰቦች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን በመፈጸም  የተጠረጠሩና  አገርን  ጉዳት ላይ የሚያደርስ ወንጀሎችን  የፈጸሙ 63 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ።

ዋና አቃቢ ህጉ እንደገለጹት በሰብዓዊ መብት ጥሰት 36 የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና 27 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ አገርን ጉዳት ላይ የሚጥል ሙስና በመፈጸም በመጠርጠራቸው መያዛቸውን ገልጸዋል ።

በሰብዓዊ መብት ጥሰትም ሆነ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ከመያዛቸው በፊት ረጅም ጊዜ በመውሰድ አስፈላጊውን መረጃን ለማሰባሰብ እንዲሁም ለማጣራት በሚስጥራዊ ሁኔታ ሲሠራ መቆየቱን  አቃቢ ህጉ ተናግረዋል ።              

በሰዎች ላይ የተፈጸሙት  የሰብዓዊ መብት ጥሰት  ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያለው መሆኑን  የገለጹት አቃቢ ህጉ ይህን የመብት ጥሰት የፈጸሙት አንዳንድ ተጠርጣሪዎች  በውጭ አገር  የሸሹ ስለመሆኑን  ተናግረዋል ።

የሙስና  ወንጀልን በተመለከተ የሜቴክና  የህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በተያያዘ  በተደረገው ምርመራ  በህዝብና በመንግሥት  ላይ ከፍተኛ  ጉዳት  የሚያደርሱ  ድርጊቶች  መፈጸማቸውን  አስረድተዋል ።

ከአምስት  ወራት  በፊት በተጀመረው  የሜቴክ  የምርመራ  ሥራ የውጭና የአገር ውስጥ ግዠዎችን እንዲሁም  ከታላቁ ህዳሴ  ግድብ ጋር በተያያዙ የተፈጸሙ ድርጊቶችን በዝርዝር ለማየት  መቻሉን አቃቢ ህጉ ገልጸዋል ።

ሜቴክ ከተቋቋመለት ደንብና አሠራር ውጪ በአጠቃላይ 37 ቢሊዮን ብር ግዢዎችን መፈጸሙን የጠቆሙት አቃቢ ህጉ ይህን ግዢ የሚፈጸመው ያለጨረታ ደላሎች እጃቸውን አስገብተው  የመንግሥት የግዠ ህግን ባላሟለ መልኩ የተፈጸመ እንደሆነ በመግለጫቸው አመልክተዋል ።

ደላሎች በተሳተፉበት ግዢ ከፍተኛ ሃብት በአገር ውስጥ ያካበቱ እንዳሉ የገለጹት አቃቢ ህጉ   በዚህ ሂደት ውስጥ  በመሳተፍም  ከፍተኛ  ሃብት  ከአገር እንዲሸሽም  ያደረጉ እንዳሉ  አቃቢ ህጉ በመግለጫው  ጠቅሰዋል ።

ሜቴክ ከተመሳሳይ ተቀሟት እስከ 40ና 50 ጊዜ ግዠ መፈጸሙን የሚያስረዳ ሰነዶች መገኘታቸውን  ይህም  በተለያዩ  መንገዶች  በተፈጠሩ  ግንኙነቶችም መሆኑን  በመግለጫቸው አብራርተዋል ።

እንደ አቃቢ ህጉ ገለጻ  ሜይቴክ ከተቋቋመበት ተልዕኮ በመውጣት  የኢትዮጵያ ሌጀስቲክስ ንብረቶች  የነበሩና ያገለገሉ ሁለት መርከቦችን መገዛታቸው  በምርመራው መጣራቱን  ገልጸዋል ።

ለእነዚህም ያገለገሉ መርከቦች ብረቱን ቆራርጦ ለመጠቀም አንዱን መርከብ በ3ነጥብ3  ሚሊዮን ዶላር  መግዛቱ  ተገልጿል  ነገር ግን  ድርጅቱ  መርከቦችን  ከህግ ውጪ  ወደ ንግድ ሥራ  እንዲገቡ ለማድረግ በአጠቃላይ  513 ሚሊዮን ብር ለጥገና ወጪ እንዲወጣ መደረጉንና  መርከቦቹ  የሚሠሩት የንግድ ሥራ  ወደ  ሜይቴክ ገቢ የማይደረግ ስለመሆኑ አቃቢ ህጉ አብራርተዋል ።

በተጨማሪም አገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመከታተል በሚል ያለንም ጨረታ በ11 ሚሊዮን 732ሺህ 520  ብር ወጪ ሜይቴክ አይሮፕላን መግዛቱን እንዲሁም ሄቴሎችን ከህግና ከደንብ ውጪ እንዲገዙ  መደረጉን  በመግለጫቸው  ገልጸዋል ።

በመጨረሻም  አቃቢ ህጉ ወንጀሎች  ሲፈጸሙ  ወደ ብሔር የሚወስዱበት አመለካከቶች መኖራቸወነ ገልጸው   ወንጀልን  በማጋለጥ ረገድ  ህብረተሰቡ  ተገቢውን ሚና ሊጫወት  እንደሚገባ  ጥሪ አቅርበዋል ።