የልብ ህመምን መለየት የሚያስችል የስማርት ስልክ መተግበሪያ ይፋ ሆነ

የልብ ህመምን መለየት የሚያስችል የስማርት ስልክ መተግበሪያ ይፋ ሆኗል፡፡

አዲስ የተፈጠረው የስማርት ስልክ መተግበሪያ አንድ ሰው ከባድ በሆነ የልብ ህመም ስለመጠቃቱም ሆነ ስላለመጠቃቱ ለመለየት የሚያስችል ነው፡፡

በመተግበሪያው ትክክለኛነት ዙሪያ የተደረገው ጥናት የልብ ህመምን ለመለየት በስፋት አገልግሎት ላይ እንደሚውለው የኤሌክትሮኒክስ የልብ መመርመሪው ኢሲጂ ሁሉ  ከባድ የልብ ህመም ምልክትን ለማወቅ እንደሚያስችል ያመላክታል፡፡

በአሁኑ ወቅት መተግበሪያው በተለይም ትኩረቱን ያደረገው ST-Elevation Myocardial Infarction ተብሎ የሚጠራውን አደገኛና ገዳይ የልብ ህመም በመለየት ላይ እንዲሆን ስለመደረጉም ነው የተጠቆመው፡፡

ይህ አደገኛ የልብ ሕመም የሚከሰተው  ዋነኛው የደም ወሳጅ ሙሉ ለሙሉ ከተዘጋ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካልታከመም ለአካል ጉዳት አለፍ ሲልም እስከ ሞት ድረስ ሊያደርስ  ይችላል፡፡

በልማዳዊው ኢሲጂ አማካኝነት አንድ ሰው የልብ ህመም እንዳለበት በተሳካ ሁኔታ ለመለየት ታካሚው ላይ12 ሊዶችን ወይም መስመሮችን መቀጠል ግድ ይላል፡፡

የእያንዳንዱ ሊዱ የሚቀጠልበት ቦታ የልብን የኤሌክትሪካል እንቅስቃሴ በተለያዩ ስፍራዎች ሆኖ ለመከታተል ይረዳል፡፡ 

ይህኛው አዲሱ መተግበሪያ ግን ከሰውነት ጋር በሚያያዙ 2 ሊዶች ብቻ እንደ ኢሲጂው ሁሉ ተመሳሳይ ተግባርን ለመከወን የሚያስችል ነው፡፡

የስማርት ስልክ መተግበሪያ ትክክለኛነት በልብ ህመም በተጠቁ 204 ታካሚዎች ላይ ተፈትሾ ስኬታማ ውጤት አስመዝግቧል፡፡

ይህ መተግበሪያ የልብ ድካምን እጅግ በጣም ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንመረምር ረድቶናል፤ የተሳሳተ የምርመራ ውጤትም አያሳይም ሲሉ የሚናገሩት የጥናት አቅራቢው ጄ ብሬንት ሙህሌስቴን ናቸው፡፡

የአዲሱ መተግበሪያ መፈጠር የልብ ህመሙ ስለመኖሩ በፍጥነት ለማወቅ የሚስችል ከመሆኑም ባሻገር ኢሲጂ መሳሪያ በቀላሉ በማይገኝባቸው ሀገራት ለሚገኙ ዶክተሮች መላ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ (ምንጭ፡-ኒው አትላስ)