አዴፓ እና አዴሃን ውህደት መፍጠራቸውን አስታወቁ

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ (አዴሃን) በጋራ ለመታገል የሚያስችላቸውን ውህደት መፍጠራቸውን ድርጅቶቹ አስታወቁ።

የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ እንዳስታወቁት ውህደቱ ሁለቱ ድርጅቶች በጋራ በመሆን ለአማራ ህዝብ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን የሚያግዝ ነው።

የሁለቱ ድርጅቶች መዋሀድ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰላም እንዲሁም የልማት ሥራዎችን በጋራ በመስራት የአማራን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

“ድርጅቶቹ በአንድ ጥላ ስር ተዋህደው መስራታቸው የክልሉን ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ለመመለስ ትልቅ አቅም ይሆናል” ብለዋል።

አዴፓ እና አዴሃን ለውህደት ያበቃቸው በድርጅቶቹ መካከል የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና የፕሮግራም ተመሳሳይነትና አንድ አይነት መሆን እንደሆነም አብራርተዋል።

“የአዴሃን አመራሮችም ሆነ አባላቱ በአዴፓ ስር ሆነውና ተዋህደው ይሰራሉ” ያሉት ኃላፊው በአዴሃን ስር የነበሩት የሠራዊት አባላትም በቀጣይ ተደራጅተው ህይወታቸውን በዘላቂነት የሚመሩበት አሰራር እንደሚዘረጋም አመልክተዋል።

ሌሎች ለአማራ ህዝብ የሚታገሉ ድርጅቶች ልዩነታቸውን እንደያዙ ሆነው ከአዴፓ ጋር በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰራም አቶ ምግባሩ አስታውቀዋል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ የውጭ ጉዳይ ፀሐፊ አቶ ማተቤ መለሰ በበኩላቸው ንቅናቄው የአማራ ህዝብ መብትን ለማስጠበቅ በኤርትራ በረሃ ለስምንት ዓመታት ሲታገል ቆይቷል።

ከቅርበ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ የተፈጠረው ለውጥና የመደመር ጉዞ ተከትሎ ንቅናቄው በአገር ውስጥ መጥቶ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቅስ በመንግስት የተደረገለትን ጥሪ አክብሮ መምጣቱን ተናግረዋል።

ንቅናቄው የአማራ ህዝብ ካለበት የዘመናት ብሶትና ጭቆና ለማላቀቅ ሲታገል መቆየቱን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ንቅናቄው እየታገለለት ያለው ዓለማ በአዴፓ እየተተገበረ በመሆኑ ውህደቱን መቀበላቸውን አስታውቀዋል።

“የድርጅት መብዛት የአማራውን ህዝብ ከማደናገር ውጭ አይጠቅመውም ” ያሉት አቶ ማተቤ ንቅናቄውና አዴፓ እንደ አንድ ሆነው በጥንካሬ የሚታገሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ለውህደት ያበቃቸውም አዴፓ መሰረታዊ የአቃፊነት ለውጥ በማምጣቱ መሆኑን ተናግረው፤ “ውህደቱ በቀጣይ የህዝቡን የልማት፣ የማንነት፣ የዴሞክራሲ እጦትና መሰል ጥያቄዎች በአንድነት ለመመለስ ጥሩ እድል ይፋጥራል” ብለዋል።

” የወልቃይትና የራያን የማንነት ጥያቄ ጨምሮ ሌሎች የልማትም ሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አልተፈቱም ” ያሉት አቶ ማተቤ ጥያቄዎችን በጋራ በመታገል መፍትሄ ለማምጣት ወደ ውህደት መምጣታቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ በኋላ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የሚባል ድርጅት እንደማይኖር ገልጸው፣ በስራቸው ሲታገሉ የነበሩ የሰራዊ አባላትም ፍላጎታቸውን መሰረት በማድረግ ሕይወታቸውን የሚመሩበት ሁኔታ እንደሚመቻች አስታውቀዋል።

የአማራ ህዝብ ጥያቄ በቀጣይም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈታ በውህደቱ ውስጥ ሆነው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በቆራጥነት እንደሚታገሉ አመልክተዋል።(ኢዜአ)