ከተማ አስተዳደሩ ከባለሃብቶችና ከተለያዩ ተቋማት የተነጠቁ ቦታዎች የሚገኙ ንብረቶችን የማንሳት እርምጃ እየወሰደ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከባለሃብቶች እና ከተለያዩ ተቋማት በነጠቃቸውና ታጥረው የቆዩ ሁሉም ቦታዎች ላይ አጥር እና ንብረት የማንሳት እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል፡፡

አስተዳደሩ ከዚህ በፊት በወሰነው መሰረት በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሣ የሚገኘው በሜድሮክ ግሩፕ የተያዘው ቦታን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ላይ በዛሬው እለት በግቢው ውስጥ ያሉ የህንጻ ማሽኖችንና ቁሳቁሶች የማሥለቀቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

የህዝብ እና የመንግስት ውስን ሃብት የሆነውን መሬት ለበርካታ አመታት ያለልማት አጥረው ይዘው የቆዩ ባለሃብቶች በተደጋጋሚ አጥረው ካስቀመጡት ቦታ ላይ ንብረቶቻቸውን እንዲያነሱ ቢጠየቁም ሳያነሱ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ የመሬት ማኔጅመንት ጽህፈት፣ የቤት የደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በመሆን ለዓመታት ያለሥራ ታጥረው የሚገኙ አጥሮችን የማፍረስ እና ንብረቶችን የማንሳት  ሥራዎችን  እያከናወነ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

በፒያሳ በሚድሮክ በታጠረው መሬት ላይ የተጀመረው እርምጃ የተሠጣቸውን ማስጠንቀቂያ ባለማክበር ንብረታቸውን ባላነሱ ሁሉም ቦታዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን የከንቲባው ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡