ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድንበር ዘለል የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል ተሰማሙ

ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድንበር ዘለል የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል ተሰማምተዋል፡፡

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በአቡዳቢ ባደረጉት ውይይት የሁለቱ አገራት ግንኙነት ያለበትን ደረጃ  በማንሳት የነበራቸውን ወዳጅነት የበለጠ በማጠናከር አገሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡

በአገር ውስጥ የተጀመረውን የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ጥረት ለመደገፍ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢኮኖሚ ላይ የሚፈፀመውን ድንበር ዘለል ወንጀሎች በጋራ ለመከላከልና ሲፈፀሙም ተቀናጅቶ ለመመርመር በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በተሳተፉበት በዚህ ውይይት በኢንቨስትመንት፣ በግዥ እና ሌሎች ተዛማጅ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል እና ለመዋጋት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ከመግባባት ደርሰዋል፡፡

በቀጣይ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚካሄዱ ጥረቶችን በህግ ማዕቀፍ ለማስደገፍ አብረው እንደሚሰሩም ተስማተዋል፡፡ (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)