የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኢ-ኮሜርስ ማዕከል በኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኢ-ኮሜርስ ማዕከል በኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የአለም አቀፍ ፖሰታል ዩኒዬን ተፈርሟል፡፡

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂነር) እና የአለም አቀፍ ፖሰታል ዩኒዬን ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ቢሻር ሁሴን የፈረሙ ሲሆን በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የቦታ አቅርቦትና መሰረተ ልማት የማሟላት ኃላፊነት ሲጠበቅበት የአለም አቀፍ ፖሰታል ዩኒዬን ደግሞ ስርዓቱን የመዘርጋት ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ለማዕከሉ ግንባታ የሚስፈልገውን የቦታ መረጣም ሆነ መሰረት ልማት በፍጥነት እንሚሟላ አረጋግጠዋል፡፡

የሚገነባው የምስራቅ አፍሪካ ኢ-ኮሜርስ ማዕከል በግል ዘርፉ መሪነት የሚተገብር እንደሆነም ተመልክቷል ፡፡

ከዚህ በፊት የምስራቅ አፍሪካ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ኬንያ ናይሮቢ ሊገነባ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መስክ እያሳየችው ባለው የተሻለ እንቅስቃሴና መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት አዲስ አበባ ውስጥ እንዲገነባ መወሰኑም ተገልጿል፡፡

በአፍሪካ ውስጥ 4 የኢ-ኮሜርስ ማዕከላት የሚገነቡ ሲሆን የምስራቅ አፍሪካው ማዕከል አዲስ አበባ እንደሚገነባ ነው የተገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚያደረገው በረራ መበራከት፣ ኢትዮጵያ በቴክሎጂ እያደገች መምጣቷ እና መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያ እንድትመረጥ አድርጓታልም ተብሏል፡፡

የማዕከሉ ኢትዮጵያ ውስጥ መገንባት ለ100 ሺዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርና በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖር እንደሚያስችልም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ምርቶች ለማንኛውም ሀገራት እንዲታዩ በማድረግ ገበያውን እንዲቀላቀሉ ያግዛል ነው የተባለው፡፡ (ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)