መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲኖር ቁርጠኛ አቋም ካለው ለመነጋገር ዝግጁ ነን- አቶ ዳውድ ኢብሳ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲኖር ቁርጠኛ አቋም ካለው ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ተናገሩ።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በዛሬው እለት በሠጡት መግለጫ፥ ኦነግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ በህጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ወደ ሀገር ከገባ አራት ወራት መቆጠራቸውን አንስተዋል።

አቶ ዳውድ በመግለጫቸው፥ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ለውጥ የመጣው የኦነግ አባላት፣ የኦሮሞ ህዝብ በተለይም ደግሞ ወጣቱ በከፈለው መስዋዕትነት ነው ብሎ እንደሚያምን ገልፀዋል።

ለውጡ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲ እንዲሸጋገር እና ሥልጣን የህዝቡ ሆኖ ህዝቡ በምርጫ ተወካዩን እንዲመርጥ እና ህዝባዊ መንግስት እንዲመሠረትም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ወስዶ እየሠራ መሆኑንም አንስተዋል።    

ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦነግ መካከል ጦርነት ነው የነበረው፤ አሁን ግን ኢህአዴግ ለውጡን ወደ ራሱ ተቀብሎ መንቀሳቀስ በመጀመሩ ጦርነት ለማቆም ተስማምተናል ይላሉ። 

የመከላከያ ሰራዊት፣ የደህንነት አገልግሎት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊሶች ፓርቲን ሲያገለግሉ ነበር ያሉት አቶ ዳውድ፤ ከመንግስት ጋር በተደረሰው ስምምነት የፀጥታ ሀይሉ ገለልተኛ እንዲሆን የመንግስት እንጂ የፓርቲ እንዳይሆን የሚለው ይገኝበታል ብለዋል።

የኦነግ ሠራዊት በፀጥታ መዋቅር እንዲካተት እና ይህንን የሚሠራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ከስምምነት እንደተደረሰም ነው አቶ ዳውድ ኢብሳ በመግለጫቸው ያነሱት።

በአሁኑ ወቅት ግን ከመንግስት ጋር የተገባው ስምምነት እየተጣሰ ነው ያሉት አቶ ዳውድ፥ በሥልጠና ያሉ የኦነግ ሠራዊት በአመራር አባላት እንዲጎበኙ አለመፍቀድ አንዱ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

አቶ ዳውድ በመግለጫቸው የመከላከያ ሰራዊት የኦነግ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ መስፈሩ ግጭት እንዲከስት ምክንያት ሆኗል ያሉ ሲሆን፥ ስሞኑንም በምዕራብ ወለጋ በመከላከያ ኃይል እና በኦነግ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መፈጠሩንም አንስተዋል።

አሁንም መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲኖር ቁርጠኛ አቋም ካለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑንም ነው ሊቀ መንበሩ አቶ ዳውድ የገለጹት።

ምርጫን በተመለከተም አቶ ዳውድ ኢብሳ፥ የቀጣዩ ምርጫ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲካሄድ እንፈልጋለን ብለዋል።(ኤፍቢሲ)