ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት የነበራት የሁለት ዓመት ቆይታ ስኬታማ ነበር – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት የነበራት የሁለት ዓመት ቆይታ ስኬታማና ብሔራዊ ጥቅሟን  ከማረጋገጥ ባለፈ  የአፍሪካን የውክልና  ድምፅን ያሰማችበት እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ  በፀጥታው ምክር ቤት የነበራትን ቆይታና በወቅታዊ ጉዳዮች  ላይ ሳምንታዊ  መግለጫ  ሠጥተዋል ።

ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት የነበራትን ተለዋጭ አባልነት ቆይታ በመጪው ታህሳስ 22 ቀን ፣2011 የሚጠናቀቅ መሆኑንም አቶ መለስ ገልጸዋል ።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የነበራት የሁለት ዓመት ቆይታ በአገሪቱ ለተጀመረው  ለውጥ ድጋፍ ማስገኘት ከማስቻሉም  በላይ የአፍሪካውያን ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲሰማ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉንም አቶ መለስ አስረድተዋል ።

በፀጥታው ምክር ቤት አባልነት ቆይታ የኢትዮጵያ  ተቀባይነት ያሳደገ በመሆኑ በተለያዩ  ጉዳዮች  ላይ አገሪቱ  የምትወስደው  አቋምም ዘላቂ  ወዳጆችና አጋሮችን ማፍራት  እንደቻለችበት  አቶ መለስ ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲኖርም ድርድሮች እንዲካሄዱ  በፀጥታው ምክር ቤቱ  ሙሉ ድጋፍ  እንዲያገኝ ያለሰለሰ  ጥረት  ስታደርግ  መቆየቷም ተገልጿል ።

 የኢትዮ ኤርትራ ድንበር በሆነው በዛላምበሳ አካባቢ መንገዶች ዳግም መዘጋቱን በተመለከተ  በጋዜጠኞች የተጠየቁት አቶ መለስ፥ “የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ዳግም መዘጋት በተመለከተ ውጭ ጉዳይ መረጃ የለውም” በሚል ምላሻቸውን ሠጥተዋል።

በሁለቱ ሀገራት ድንበር ጋር በተያያዘ ያለውን መረጃ በሌላ ጊዜ መልስ እንደሚሰጡበትም  ገልጸዋል ።

በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር በመሆን  የተሾሙት አምባሳደር ሰመረ ርዕሶም በዛሬው ዕለት  የሹመት ደብዳቤዎችን ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ማቅረባቸውን አቶ መለስ አስታውቀዋል።