ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምን ፣ ዴሞክራሲና ልማትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሁኔታ ሲፈጠር መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ በዛሬው ዕለት ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሠጡት ማብራሪያ እንደገለጹት መንግሥት በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ምህዳሩ ለማስፋት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል ።
መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የወሰነው በአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የለምንም እንቅፋት እንዲረጋገጥ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ የፖለቲካው ምህዳርን ይበልጥ እንዲሰፋ ለማድረግ ግን የሁሉም አካላት ትብብር አስፈላጊ ነው ብለዋል ።
ህዝብን አስተባብሮና አንድ አድርጎ መታገል የተለየ የፖለቲካ አመራር ጥበብን የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ የትኛውም የፖለቲካ ኃይል የአገሪቱ ሰላምን ፣ ዴሞክራሲንና ልማትን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ልታገል ካለ ግን መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል ።
የኢትዮጵያን አንድነት የሚገዳደር ጉዳይ ላይ የሚሠራ ኃይል በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንዳወጀ የሚቆጠር በመሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች ፣ ግለሰቦችና ፓርቲዎች አገሪቱን አደጋ ላይ ከሚጥል ተግባር ሊቆጠቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
መንግሥት የማይተች አካል አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የተቃውሞ ድምጽን ማሰማትና አገራዊ አንድነትን መገዳደር የተለያዩ ተግባራት መሆናቸውን ተናግረዋል ።
መንግሥት ከ 20 በላይ የታጠቁና ያልታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ የፈቀደው የአገሪቱን ሁለንተናዊ ለውጥ ይበልጥ ለማፋጠን በማሰብ መሆኑንና ይህም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትልቅ ድል መሆኑን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል ።
የትኛውም አካል ለመንግሥት የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለማድረግ የሓሳብ ትግል በማድረግ ብቻ የሚፈጸምና በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ አካላት ብቃት ስላለኝ ታግዬ አሽንፋለው የሚል አስተሳሰብን መፍጠር ይኖርባቸዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጥ የሪፎርም ሥራ ከሠሩ ተቋማት ውስጥ የመከላከያ ኃይል አንዱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ መከላከያ በብሔር ተዋጽኦን በመጠበቅ ፣ በአገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶችን በማብረድ በኩል መልካም ሥራን በማከናወኑ ሊወቀስ አይገባም ብለዋል ።
በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች የፖለቲካ ነጋዴዎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ የሓሳብ ፍጭት እንጂ በድንጋይ ውርወራ ላይ መሠማራት የተማረ ሰው መገለጫ ባህሪ አለመሆኑን አስረድተዋል ።
በአገሪቱ እየታየ ያለውን ህገ-ወጥ የመሣሪያና የገንዘብ ዝውውርን በተመለከተ ኢህአዴግ በተሃድሶው ያየው ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች እንዲገቡ በማድረግ ችግር ለመፍጠር የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ገልጸዋል ።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሉዓላዊ አገር እንጂ ሉዓላዊ ክልል የለም ስለዚህም ሁሉም ዜጋ በፈለገው ክልል ና ቦታ ተዘዋውሮ መሥራትና ህይወቱን መምራት የሚችልበት ሁኔታም መፈጠር እንዳለበት ጠቅላይ ሚንስትሩ አጽዕኖት ሠጥተው ተናግረዋል ።
በአገሪቱ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆምና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሰላም ሚኒስቴር ተቋቁሞ የአገር ሽማግሌዎች ፣ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን በጋራ እየሠሩ ስለመሆኑ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል ።
በመጨረሻም በወንጀል ተጠርጥረው ለፍርድ እየቀረቡ ያሉ ግለሰቦች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተጠብቆ ጉዳያቸው እየታየ መሆኑንና ማንኛውም ዜጋ ወንጀል ፈጽሞ የትም መደበቅ እንደማይችልና ቢደበቅ እንኳን ህሊናው ነጻ እንደማይሆን ተናግረዋል ።