የኦሮሚያ ክልል ከኢንቨስትመንት መሬት አሰጣጥና ፍሰት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ውሳኔ አሳለፈ

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ካቢኔ ከኢንቨስትመንት መሬት አሰጣጥና ፍሰት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሁለት ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ምክር ቤቱ ትላንት 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በዚህም በክልሉ የኢንቨስትመንት መሬት አሰጣጥን ደረጃ የሚወስንና ፍሰቱን ተደራሽና የተቀናጀ ማድረግ በሚያስችሉ  ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው አስታውቀዋል።

ረቂቀ ደንቦቹ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የኢንቨስትመንት ፍቃድ አሰጣጥ ወጥነት፣ ተመጋጋቢነትና የግብዓት አቅርቦት ተደጋጋፊነት ችግሮችን መፍታት እንደሚያስችሉም ሀላፊው ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የፍትሃዊ ተደራሽነትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ውስንነቶች ከመሠረቱ ለመቅረፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማሪም ደንቦቹ በዘርፍና በኢንቨስትመንት ልማት ኮሪደር እንዲሰበሰቡ የሚረዳ መስፈርት ያላቸው በመሆኑ  ባለሃብቱን በመሳብ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚረዱ ናቸውም ብለዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ዙሪያ ባሉ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስር ስራዎች ጠንካራና ግልጽነት ያለው አሠራር ለመዘርጋትም አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ተነግሯል፡፡

እንዲሁም ውስን የሆነውን የመሬት ሀብት ብክነት በማስቀረት የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት በሚያበረታታ መልኩ የተዘጋጁ ናቸው፡፡

ደንቦቹ በተለይ አርሶ አደሩንና በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው በተለያዩ ዘርፎች የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ወደ ኢንቨስትመንት በመግባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)