ዜጎች ነጻ የትምህርት እድል በሚል ያለበቂ መረጃና ፍቃድ ወደ ቻይና በመሄድ ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ ናቸው-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ዜጎች ነጻ የትምህርት እድል በሚል ያለበቂ መረጃና ፍቃድ ወደ ቻይና በመሄድ ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው አስታወቁ፡፡

ዜጎቹ በህገወጥ ደላሎች በኩል የሚነዛው የተሳሳተና የተጭበረበረ የነጻ የትምህርት ዕድል ቅስቀሳ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የህገወጥ አደንጻዥ ዕጽ በተለይም ጫት ዝውውር መረብ ሰለባ መሆኑን አስታውቀዋል።

እስካሁን ከ47 በላይ ዜጎቻችን በቻይና ልዩ ልዩ ግዛቶች አደንዛዥ ዕጽ በማዘዋወር እና ጫት በማስመጣት፣ በግድያ ወንጀል፣ በስርቆትና ሳይበር ክራይም፣ ያለ መኖሪያ ፍቃድ ረዥም ጊዜ በመቆየት፣ ያለስራ ፍቃድ በመስራት ወንጀሎች የታሰሩ ሲሆን የተወሰኑት በተጠረጠሩት ወንጀል ተፈርዶባቸው የእርምት ጊዜያቸውን እየተከታተሉ እንዲሁም የተወሰኑት በተጠረጠሩበት ወንጀል በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ከነጻ የትምህርት ዕድል ጋር በተየያዘ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ ጫትን ጨምሮ አደንዛዥ ዕጽ በቻይና በህግ የተከለከለና የሞት ፍርድን ጨምሮ እስከ ዕድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑ በግንዛቤ እንዲያዝ በመግለጫው ተመልክቷል።

በጉዳዮ ዙሪያ መንግስት ቤጂንግ በሚገኘው ኤምባሲና በአራቱ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በኩል ከቻይና ምንግስት ጋር በመነጋገር ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት እየሰራ መሆኑንም አቶ ነቢያት ጠቁመዋል።

በተያያዘ ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም በጅቡቲ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በምትገኘው ኦቦክ አስተዳደራዊ ክልል ጎዶሪያ በሚባል ስፍራ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ወደ የመን ለመሸጋገር ሲሞክሩ የነበሩ 57 ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

መንግስት ለችግሩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ነቢያት በዚህ ሳምንት 1 ሺህ 40 ዜጎች ከሳኡዲ አረቢያ፣ 1415 ከፑንትላንድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።

(ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት)