ላለፉት ሰባት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የደቡብ ኢትዮጰያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢህዴን ከፍተኛ አመራሮች መድረክ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታና ድርጅቱ ባስጠናው የክልልነት ጥያቄ ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ተጠናቀቀ።
በምክክር መድረኩ የሰባት ቀናት ቆይታ ዙሪያ የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ለአመራር መድረኩ በቀረቡ አጀንዳዎች ዙሪያ የተደረገው ውይይት ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ነበር።
በሀገሪቱ ተጀመረውን ለውጥ በድርጅት ውስጥም ሆነ በውጪ ሊያደናቅፍ የሚያስችል የአመለካከት መዛባት ያለበት በመሆኑ ይህን በማረም የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ስምምንት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር ለማስቆም የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑን በጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ የተጀመረው ሰላምና ጸጥታን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመድረኩ አቋም እንደተያዘ ተናግረዋል።
የኮማንድ ፖስቱ ተግባር የህዝብ የነቃ ተሳትፎ እንዲጎለብት በማድረግ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ እንዲሆን የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን ህጋዊ መስመር ለማስያዝ በተወሰኑ አካባቢዎች የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ሌሎችም በህጋዊ መንገድ ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ አመራሩ በትኩረት ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።
የህዝብ የመብት ጥያቄዎች በሆታና በግርግር ለማዛባት የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ አመራሩ ይህን በተመለከተ የጋራ አቋም መያዙን ገልጸዋል።
በክልል የመደራጀት ጥያቄ ህገ-መንግስታዊ ቢሆንም በአንድ ጊዜ በርከት ያለ የክልልነት ጥያቄ በመቅረቡ በጥንቃቄ ካልተያዘና ካልታየ የሚያስከትለውን አደጋ ለማስቀረት ደኢህዴን ባስጠናው ጥናት ዙሪያ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።
በጥናቱ ዙሪያም የጋራ መግባባት ላይ እንደተደረሰና መላው የክልሉ ህዝብ ውይይት ሊያደርግበት እንደሚገባ በመድረኩ መወሰኑን ተናግረዋል።
“በድርጅቱ ዙሪያ በተለያዩ ምክንያቶች በህዝቡ ዘንድ እየተሸረሸረ የመጣውን ዕምነት ለመመለስ አመራሩ ግልጽነትን በማስፈን ተግባሩን ማከናወን ተገቢ መሆኑን መድረኩ አምኖበታል” ብለዋል።
መድረኩ በቆይታው በአመራሩ ዘንድ መነሳሳትና መግባባት የሰፈነበት አንድ አቋም ይዞ የወጣበት በመሆኑ መላው የክልሉ ህዝብ ከድርጅቱ ጎን እንዲሰለፍ ለማድረግ የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ሞገስ ገልጸዋል።